ኢትዮጵያ ከአለምአቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች -- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከአለምአቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች -- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከአለምአቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
አምባሳደር ምስጋኑ ከአለምአቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቶ ዌንፎል ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸው በድርጅቱ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ስላለው ግንኙነትና ይሄንንም ማጠናከር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነበር።
አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድ እንዲሁም የሃገር ውስጥ ተፈናቃይ ያሉባት ሃገር እንደመሆኗ ከአለምአቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በጠንካራ ትብብር ትሰራለች ብለዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ፍልሰት የደቀነውን ችግር ለመቅረፍ ድርጅቱ የሚሰራቸውን ስራዎች የኢትዮጵያ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚደግፍ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋግጠዋል።
በተለያዩ ግጭት ባለባቸው ሃገራት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ለመደገፍ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም ውይይት አድርገዋል።
የአለም አቀፍ ፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቶ ዌንፎል ድርጅታቸው ለሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ለውጭ ፍልሰተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዋና ተወካይዋ ኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት የሚሰጣት ሃገር መሆኗን በመጥቀስ የውጭ ፍልሰተኞችን በመቀበል ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተች መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት እና አለምአቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት መካከል እያደገ የመጣ ግንኙነት መኖሩን አስታውሰው ፤ በቀጣይም ከፍልሰት ጋር በተያያዙ ማዕቀፎች ትብብራቸው እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።