የአውሮፓ ሕብረት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ሕብረት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ
አዲስ አበባ ግንቦት 11 / 2015 (ኢዜአ)፡-የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ለመልሶ ግንባታና ማገገሚያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
ሕብረቱ በኢንቨስትመንት በኩል ያለውን ትብብርም የበለጠ ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሕብረቱ አባል አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ጠንካራና ታሪካዊ ግንኙነት አውስተዋል።
የሕብረቱ አባል አገራት ከኢትዮጵያ ጋር በምጣኔ ሃብትና በልማት ትብብር ዘመናትን የተሻገረ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንዳላቸውም ጨምረዋል።
ሕብረቱ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት እያከናወነው ያለውን ተግባር ህብረቱ አበክሮ እንደሚደግፍ አስረድተዋል፡፡
በምጣኔ ሃብት ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ለኢንቨስትመንት ዕድገት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ፍሰቱን ለመጨመር የሚያከናውናቸውን ተግባራትን ሕብረቱ እንደሚያግዝ አረጋግጠዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በስፋት ለመሰማራት ዝግጁ ናቸው።
በኢትዮጵያ በርካታ የአውሮፓ ካምፓኒዎች እንደሚገኙና የስራ ዕድል እንደፈጠሩ አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በቀጣይ ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት ወደ ሀገሪቱ እንዲገባና በርካታ የስራ ዕድል እንዲፈጠር ለማስቻል ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።