የበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን ያመላከተ ነው - የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን ያመላከተ ነው - የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015 (ኢዜአ)፦ የበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን ያመላከተ ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የ2015 በጀት ዓመት የሶስተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እየተገመገመ ነው።
በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፤ ኢኮኖሚው በርካታ የውጪ እና የአገር ውስጥ ጫናዎችን ተቋቁሞ በአፍሪካ ፈጣን የሚባል ዕድገት በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠንካራ የዕድገት አፈጻጸም እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው ውጤቱ በዓለም አቅፍ የልማት አጋሮች ጭምር የተረጋገጠና ይፋ የሆነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በፕሮጀክቶች አፈጻጸም የተሻለ ውጤት መመዝገቡን የገለጹት ሚኒስትሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸምም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፐፕሊክ ፋይናንሱ የገቢ አቅምን ከማመንጨት አንጻር የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱንም ነው የገለጹት።
መሰረታዊ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን ከመከተል አኳያም ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
እንደ አጠቃላይ የበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን ያመላከተ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ኢኮኖሚው የተሻለ ዕድገት ማስመዝገቡን ገልጸው አሁንም የኑሮ ውድነት ትልቅ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።
የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በቀጣይ ሰፊ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ሴክተሮች ውጤታማ ስራዎች ቢከናወኑም ከውጪ እና ከውስጥ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ፈታኝ እንደነበሩም አስታውሰዋል።
ይህን ለማካካስም የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሁለት አካል የሆነ ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም የሚተገበር የሶስት ዓመት የመንግስት የልማትና የኢንቨስትመንት ዕቅድ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በመቋቋም የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡
በሚቀጥለው ዓመት በጀት ላይ የአገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸው፣ ወጪዎች በመሰረታዊ የልማት እና የአገልግሎት ስራዎች ላይ ትኩረት እንደሚደርጉም ጠቁመዋል፡፡