ቀጥታ፡

ማኀበሩ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ አምቡላንሶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ  ተረከበ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ  ቀይ መስቀል ማኀበር ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ አምቡላንሶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች  ድጋፍ  ተረከበ።

 ኮሚቴው ከ28 ሚሊዮን ብር  በላይ የሚያወጡ 14 አምቡላንሶች፣ 18 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ቀላል ተሽከርካሪዎችና  8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ታአ በዚህ ወቅት  እንደገለፁት፤ በድጋፉ የተገኙት ተሽከርካሪዎች ማኅበሩ የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት የሚረዳው ነው።


 

ዛሬ ኮሚቴው ያደረገው ድጋፍ የማህበሩን የአምቡላንሶች ቁጥር ወደ አራት መቶ አርባ አራት ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ማህበሩ ከአጋር አካላቶች ጋር በትብብር እያካሔደ ያለውን ሕይወት የማዳን ስራ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

ድጋፉ በተለይ የመጀመሪያ ህክምናና ቅድመ ሆስፒታል እንክብካቤ ለመስጠት የሚገጥመውን የቁሳቁስና ሌሎች የአቅርቦት ችግሮች ለመፍታት ያስችላል ነው ያሉት ።

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ተወካይ ኒኮላስ ቫንራክ በርክክቡ ወቅት እንደገለፁት፤ አምቡላንሶቹ  በመጠለያ ጣቢያዎችና በሆስፒታሎች ያሉ ዜጎችን ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ ይረዳል።

 

 

 

                                      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም