አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ከጀጁ ደሴት ገዢ ኦ ያንግ ሁን ጋር በተለያዩ መስኮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ውይይት አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ከጀጁ ደሴት ገዢ ኦ ያንግ ሁን ጋር በተለያዩ መስኮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ውይይት አደረጉ
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015(ኢዜአ)፦ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ከጀጁ ደሴት ገዢ ኦ ያንግ ሁን ጋር በተለያዩ መስኮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ውይይት አድርገዋል።
በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ከጀጁ ደሴት ገዢ ኦ ያንግ ሁን ጋር በኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም በባህልና በአካባቢ ጥበቃ መስኮች ያለውን አቅም በማስተባበር በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
አምባሳደር ደሴ ኢትዮጵያ አፍሪካን ከመካከለኛው ምስራቅና ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ለማገናኘት ስትራቴጂካዊ ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።
በዚህም በርካታ የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ከአፍሪካ ጋር ያለውን ትብብር ለማስፋፋት ኢትዮጵያን መጠቀም መልካም አጋጣሚ እንደሆነም አምባሳደሩ ጨምረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና የብዘሃ-ህይወት መገኛ እንዲሁም በዩኔስኮ የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን አስረድተው እነዚህም ሀገሪቱን ተስማሚ የቱሪስት መዳረሻ ያደርጓታል ብለዋል።
በቱሪስት ፍሰቷ የምትታወቀው የደቡብ ኮሪያዋ ጀጁ ደሴትም ከኢትዮጵያ ጋር በቱሪዝም ዘርፉ በርካታ የሚያመሳስላት ነገር እንዳለና በመስኩ ትብብር መፍጠር ለሁለቱም ወገኖች የጋራ ጥቅም እንደሚሆን አብራርተዋል።
በመሆኑም የደሴቲቱ ገዢ ኦ ያንግ ሁን በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች አልያም ክልሎች ጋር በትብብር ለመስራት አማራጮችን እንዲያዩም ጠይቀዋል።
የደሴቲቱ ገዢ ኦ ያንግ ሁን በበኩላቸው በኢትዮጵያ እና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት አስታውሰዋል።
የደሴቲቱ ገዢ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በደሴቲቱ ያደረጉትን ጉብኝት አድንቀው በሁለቱ ሀገራት መካከል በኢኮኖሚ ልማት፣ በቱሪዝምና በባህል እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ መስኮች ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል።
የደሴቲቱ ገዢ ኦ ያንግ ሁን አክለውም ጀጁ ደሴት ከአዲስ አበባ ጋር ተግባራዊ የልምድ ልውውጥ እና ትብብር ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።