ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በዘጠኝ ወራት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015 (ኢዜአ):- በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጽህፈት ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

ለግድቡ ግንባታ የህብረተሰቡን ተሳትፎና እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን በማስመልከት ኢዜአ ከጽህፈት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር ጋር ቆይታ አድርጓል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በሀገር ውስጥና በውጭ ካሉ ወገኖች 1 ነጥብ  5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ1  ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

ከቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ ከ8100 ኤ አጭር የፅሁፍ መልእክት፣ ከፒን ሽያጭ እና ሌሎችም አማራጮች ገቢው መሰብሰቡንም አስረድተዋል። 

የግድቡን ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ መቀጠሉን የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሯ ከፍፃሜ ለማድረስ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 18 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው መሰል ድጋፍና እገዛዎችን በማጠናከር የግድቡን ግንባታ ፍፃሜ በጋራ እውን እናድርግ ብለዋል።

በመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የግንባታ መሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግንባታ ሂደት 12ኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም