ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመጪው ትውልድ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለመ ነው- የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015 (ኢዜአ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመጪው ትውልድ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለመ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸዉ ለምዕራፍ አንድ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬታማነት የአርሶና አርብቶ አደሩ በባለቤትነት መሳተፍ ጉልህ ድርሻ ነበረው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ግምገማ "አረንጓዴ አሻራችን ለዘላቂ ልማታችን" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።


 

ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 25 ቢሊየን ችግኝ በመትከል የመጀመሪያው ምዕራፍ በስኬት ተጠናቋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ፤ ኢትዮጵያ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች፣ በርካታ አምራች ሃይልና ሌሎች ሃብቶች እንዳላት ይናገራሉ። 

ሆኖም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የአፈር መሸርሸር፣ የብዝሀ ህይወት መመናመንና የጎርፍ አደጋ እየፈተናት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም  የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከታቀደው በላይ 25 ቢሊየን ችግኝ በመትከል በስኬት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን ጭምሮ በሁሉም መስኮች ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበች መሆኑን ተናግረው ከስንዴ ተመጽዋችነት ወደ ውጭ ገበያ አቅራቢነት መሸጋገሯ ለስኬቱ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የሌማት ትሩፋት እና ሌሎችም የሚታዩ ውጤቶች መሆናቸውን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለመ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በመሆኑም ይህንን በመገንዘብ በቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለሚያስጀምሩት ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬት ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል ነው ያሉት።

በመርሃ ግብሩ ችግኝ ለምን እንደምንተክል በመረዳት፣ ለመትከል በመዘጋጀት፣ በመትከል፣ በመንከባከብና በመጠቀም አምስቱ "መ" ዎችን ገቢራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።


 

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ለምዕራፍ አንድ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬታማነት የአርሶና አርብቶ አደሩ በባለቤትነት መሳተፍ ጉልህ ድርሻ ነበረው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ አጀንዳ መሆኑን በመረዳት በጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ በሶማሊያና ደቡብ ሱዳን መሪዎችን በማስተባበር ከ223 ሺህ በላይ ችግኞችን እንዲተከሉ መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግቧል ብለዋል።

በየዓመቱ ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ በመሸርሸር ይባክን የነበረውን 130 ቶን አፈር ወደ 42 ቶን ዝቅ እንዲል ማድረግ መቻሉንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በዚህም የአፈር ለምነት ጨምሯል፣ የሰብልና እንስሳት ምርታማነት አድጓል፣ የወል የተፋሰስ ልማት እድገትና መሻሻል አሳይቷል ብለዋል።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኦሲሜን ዲዮን በኢትዮጵያ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ኢትዮጵያ እያደረገች ላለው የላቀ አስተዋጽኦ የዓለም ባንክ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም