በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታ በቦክስ ስፖርት ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው- የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታ በቦክስ ስፖርት ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው- የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015 (ኢዜአ) በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታ በቦክስ ስፖርት ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ገለጸ።
በኦሊምፒክ ጨዋታ በአትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያ ከተሳትፎ በላይ ከፍተኛ ውጤት የምታገኝበት ሲሆን
ብስክሌት፣ ቦክስ፣ ውሃ ዋና፣ ወርልድ ቴኳንዶና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
ኢትዮጵያ በ2020 ኦሊምፒክ በአትሌቲክስ፣ በወርልድ ቴኳንዶ፣ በብስክሌትና በውሃ ዋና መሳተፏ ይታወሳል።
በቦክስ ስፖርት በተለያየ ጊዜ ተሳትፎ ቢኖርም ባለፉት አራት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ግን ማጣሪያውን ማለፍ ባለመቻል ኢትዮጵያ ከተሳትፎ መራቋን አስታውሰዋል።
በመሆኑም በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታ በቦክስ ስፖርት ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ስንታየሁ ተስፋዬ፤ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ለኦሊምፒኩ በቦከስ ውድድር ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ ዝግጅት ተጀምሯል ብለዋል።
የቦክስ ብሔራዊ ቡድኑ ከሚያዝያ 22 እስከ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም በኡዝቤኪስታን በተካሄደው የዓለም ቦክስ ሻምፒዮና ጠንካራ ተሳትፎ አድርጓል ብለዋል።
በሻምፒዮናው ከ107 ሀገራት የተውጣጡ ከ530 በላይ ቦክሰኞች መሳተፋቸውን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ በውድድሩ 16 ውስጥ መግባቷን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በውድድሩ የተመዘገበው አበረታች ውጤት በቀጣይ ለሚደረጉ ውድድሮች ጥሩ ልምድ የተገኘበት መሆኑን ገልጸው በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ የተሻለ ውጤት ለማስመዘገብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በኦሊምፒክ ጨዋታ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ በሚቀጥለው ወር ሀገር አቀፍ የክለቦች ቦክስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመው በኡዝቤኪስታን በተካሄደው ውድድር የተመረጡ ቦክሰኞችና ሌሎችም የብሄራዊ ቡድን አባላት ሚመረጡበት እንደሆነ ነው የገለጹት።
በዓለም ቦክስ ሻምፒዮና ከተሳተፉ ተወዳዳሪዎች በተጨማሪ የተሻለ አቅም ያላቸው አትሌቶች ከተገኙ በማጣሪያው እንዲሳተፉ የሚመረጡበት እድል እንዳለም አንስተዋል።
በፓሪሱ ኦሊምፒክ በቦክስ ስፖርት መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ውጤት ለማምጣት ታቅዶ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል።