ቀጥታ፡

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ድጋፍና ክትትላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን  -  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት 

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተከናወኑ ላሉ ተግባራት ድጋፍና ክትትላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።  

የምክር ቤቱ አባላት በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ የሚገኘውን የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽን ጎብኝተዋል።

በግብርና ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎች፣ የምርምርና ፈጠራ እንዲሁም የግብርና ፋይናንስ በአውደ-ርዕዩ ለእይታ ቀርበዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ በግብርና ሳይንስ የደረሰችበትን ደረጃ መገንዘብ እንደቻሉ ገልጸዋል።
 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወጌ ቁፋ፤ በአገር ውስጥ በሚገኝ የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን የሚያስችሉ የሳይንስ ውጤቶችን መመልከታቸውን ጠቁመዋል። 
 

ሌላኛው የምክር ቤት አባል አበባው ደሳለው፤ በስንዴ፣አረንጓዴ አሻራ፣ግብርና ቴክኖሎጂና ሌሎች ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ያሉበትን ደረጃ ለመገንዘብ መቻላቸውን ገልጸዋል።
 

የምክር ቤት አባሏ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ቀደም ሲል የነበረችበትና አሁን የደረሰችበትን ደረጃ ለመረዳት እንደቻሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የዘርፉን ምርታማነት ለመጨመር እያከናወነች ያለውን ተግባር ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እንደሚያግዙ የምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ዘርፉን በማዘመን፣ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ፣ ምርታማነትን ለመጨመር እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በችግሮች ውስጥ ብታልፍም በግብርናው ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቧን  ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እየሄደችበት ያለውን አቅጣጫ፣እንደ አገር አቅዶ ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳይ ነው ብለዋል።

መንግስት በግብርናው ዘርፍ ለሚያከናውነው ተግባር ችግር ያለባቸው አዋጅና ፖሊሲዎችን በማሻሻልና በማውጣት እንደሚሰራም ተናግረዋል። 

"ከቤተ-ሙከራ ወደ አዝመራ" በሚል መሪ ሀሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው አውደ-ርዕይ ሚያዝያ 30 ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ መከፈቱ ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም