ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ወደ ፌደራል ፖሊስ ለተቀላቀሉ የቀድሞ ልዩ ሀይል አባላት የአቀባበል እና የስልጠና መርሃ ግብር አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ወደ ፌደራል ፖሊስ ለተቀላቀሉ የቀድሞ ልዩ ሀይል አባላት የአቀባበል እና የስልጠና መርሃ ግብር አስጀመሩ
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ወደ ፌደራል ፖሊስ ለተቀላቀሉ የቀድሞ ልዩ ሀይል አባላት የአቀባበል እና የስልጠና መርሃ ግብር አስጀመሩ።
መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ነው የተካሄደው።
በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች ተገኝተዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የፌዴራል ፖሊስን የመረጡ የቀድሞ ልዩ ሀይል አባላት በክልል ደረጃ ለአገራቸው ሲያበረክቱ የነበረውን አስተዋጽኦ የፌዴራል ፖሊስ አባል በመሆንም መድገም እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
መንግስት ጠንካራ የፖሊስ እና የመከላከያ ሃይል እንዲኖር የክልል ልዩ ሃይል የነበሩ አካላት መልሶ የማደራጀት ውሳኔ በመወሰን ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
አባላቱ በፖሊስ ዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ህዝቡን በቅንነት፣ በታማኝነት እና በሙያዊ ስነ-ምግባር የሚያገለግሉበትን እውቀት እና ክህሎት እንደሚጨብጡም ገልጸዋል።
የስልጠና ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ ከብሔር፣ ከሃይማኖት እና ከፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ማህበረሰቡን በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የፖሊስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው አባላቱ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለቀጣይ ተልዕኮ ብቁ የሚያደርጋቸውን ስልጠና እንደሚያገኙ ገልጸዋል።
ስልጠናው በፖሊስ ዶክትሪን፣ በፖሊሳዊ ስነ-ምግባር፣ በወንጀል መከላከል እና በሌሎችም ዘርፎች የሚሰጥ መሆኑን በመጠቆም።
ፌደራል ፖሊስን የተቀላቀሉ አባላት በዩኒቨርስቲው በሚኖራቸው ቆይታ ስነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ ስልጠናውን ለመከታተል ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ከስልጠናው በኋላም አገርና ህዝብን በሚጠበቅባቸው ሁሉ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።