ቀጥታ፡

ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የማዘመን ተግባር በትኩረት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ

አዲስ አበባ  ግንቦት 10/2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለገቢና ወጪ ጭነቶች ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት አሰራሮች በቴክኖሎጂ የማዘመን ተግባር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ገለጸ። 

ተቋሙ የ2015 ዓ.ም የደንበኞችና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ዘርፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ በተጣለው ገደብ ሳቢያ የንግድ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን አንስተዋል።

በዚህም በዘርፉ በከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ፣ በሰው ኃይል እጦትና በአዲስ መልክ በወጡ የአካባቢ ጥበቃ ሕግጋትና ደህንነት ስጋት ለፈተና ተጋልጦ የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በሩሲያና ዩክሬን መካከል ያለው ጦርነት በወጪ ንግድ አቅርቦት ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን አመልክተዋል።

በተጨማሪም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነትም በተለይም በሰሜንና ምዕራብ የአገሪቷ ክፍሎች የአፈር ማዳበሪያን በየብስ ትራንስፖርት ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።

ይህም ሆኖ ተቋሙ እነዚህን ዓለም አቀፍና አገራዊ ተግዳሮቶች በመቋቋም በተያዘው በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ወሳኝ በሆኑ በማጓጓዣ(ሺፒንግ)፣ጭነት ማስተላለፍ፣በወደብና ተርሚናል አገልግሎት የኦፕሬሽን ዘርፎች ስኬታማ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ለኢትዮጵያ ለገቢም ሆነ  ለወጪ ጭነቶች  አስፈላጊውን የሎጂስቲክስ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንና ተቋሙ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሻሻል ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።                   

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ደንበኞች  በበኩላቸው፤ ተቋሙ እያደረገ ያለው ለውጥ የሚበረታታ መሆኑን በማንሳት ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ የአገልግሎት መስተጓጎል በቋሚነት መፍትሔ እንዲያገኝ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፤ ደንበኞች ያነሱትን ችግር በማጣራት አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተቋሙ አገልግሎቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለመውሰድ በጀመረው እንቅስቃሴ የድሬደዋ ወደብና ተርሚናል የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጠናቆ ወደ ስራ የገባ መሆኑም በመድረኩ ላይ ተመላክቷል። 

እንዲሁም በአገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርት እውን ለማድረግ እንዲቻል ኢትዮ-ፌሪስ ጣና የተሰኘ ቅርንጫፍ በባህር ዳር ሀይቅ ላይ በመክፈት ወደ ስራ ለማስገባት የመሰረት ድንጋይ መጣሉ ተገልጿል።

በየብስ ትራንስፖርት አቅሙን ለማጎልበት 85 ከባድ ዘመናዊ የጭነት ተሽከርካሪዎች ግዥ በመፈጸም ወደ  ስራ እንዲገቡ መደረጉ ተጠቁሟል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም