ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ተገኝቷል - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ተገኝቷል - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2015 (ኢዜአ)፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገበው አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ የተቀመጠው የ7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት እንደሚሳካ አመላካች መሆኑም ተገልጿል።
የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እየተገመገመ ነው።
በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ የበጀት ዓመቱን ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዓለም አቀፍ ገበያ ያሉ አለመረጋጋቶችን በመቋቋም በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ለአብነትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ተገኝቷል ነው ያሉት።
ይህም የዕቅዱን 71 በመቶ መሳካቱን የሚያመላክት ሲሆን፤ በወጪ ንግድ ከተገኘው ገቢ የግብርና ዘርፍ ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛል ብለዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቡና ምርት 897 ሚሊየን ዶላር መገኘቱንም በአስረጂነት አቅርበዋል።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሳይጨምር በግለሰቦች በሃዋላ 3 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱንም እንዲሁ።
የገቢ ምርቶችን በመተካት ረገድም የተሻለ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰው፤ ስንዴና የቢራ ብቅል ገብስ ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ መተካት መቻሉን ተናግረዋል።
በተለይ በቢራ ብቅል ገብስን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉ ከ244 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።