ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ‘ገርልስ ኢፌክት’ ከተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም የኢትዮጵያ ቢሮ አመራሮች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ‘ገርልስ ኢፌክት’ ከተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም የኢትዮጵያ ቢሮ አመራሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2015(ኢዜአ):- ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትን ለማጥፋት ከሚሰራው ‘ገርልስ ኢፌክት’ ከተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም የኢትዮጵያ ቢሮ አመራሮች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይቱ ተቋሙ በኢትዮጵያ ሴቶችን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ማህበረሰባዊ እሳቤዎች ላይ ለውጥ ማምጣትና ታዳጊ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮግራሞችን ቀርጾ በሚሰራበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አመልክቷል።
‘ገርልስ ኢፌክት’ እ.አ.አ 2008 የተመሰረተ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት የሚገኙ ታዳጊ ሴቶች(ከ10 እስከ 18 የእድሜ ክልል የሚገኙ) ከድህነት እንዲላቀቁ አላማ አድርጎ የሚሰራ ነው።