የፖሊስ መኮንኖች የቀሰሙትን እውቀት ከክህሎት ጋር በማዋሀድ የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ ይገባል - ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የፖሊስ መኮንኖች የቀሰሙትን እውቀት ከክህሎት ጋር በማዋሀድ የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ ይገባል - ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2015(ኢዜአ)፦ የፖሊስ መኮንኖች የቀሰሙትን እውቀት ከክህሎት ጋር በማዋሀድ የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከኢንስፔክተር ወደ ዋና ኢንስፔክተር ማዕረግ የተሸጋገሩ 108 መኮንኖችን በዛሬው እለት አስመርቋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ በመገኘት የሥራ መመሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የፖሊስ መኮንኖች የቀሰሙትን እውቀት ከክህሎት ጋር በማዋሀድ የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የፖሊስ መኮንኖቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ባገኙት እውቀት በሚሰማሩበት የኃላፊነት ቦታ ሁሉ አገራዊና ሕዝባዊ አደራቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው፤ ምሩቃን በወንጀል መከላከል ዘርፍ በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡
ምሩቃኑ በሦስት ወራት የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በፖሊስ ሥነ-ምግባር፣ በወንጀል መከላከልና ምርመራ፣ በሳይበር ወንጀል ደኅንነት፣ በወንጀልና የትራፊክ አደጋ መከላከልና ሌሎች የትምህርት ዘርፎች ሥልጠና መከታተላቸው ተገልጿል።
የፖሊስ መኮንኖቹ ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከድሬደዋ ፖሊስ የተውጣጡ መሆናቸው ተገልጿል።