አምባሳደር እፀገነት ይመኑ በዩጋንዳ ከናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ፀሀፊ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር እፀገነት ይመኑ በዩጋንዳ ከናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ፀሀፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2015(ኢዜአ)፦በዩጋንዳ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር እፀገነት ይመኑ የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ፀሀፊ ከሆኑት ሲይልቪስተር አንቶኒ ጋር በካምፓላ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ኢኒሼቲቩ እስከ አሁን ባከናወናቸው የስራ እንቅስቃሴ እና ቀጣይ መሰራት ባለባቸው የትብብር መስኮች ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
አምባሳደር እፀገነት ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የአባይ ተፋሰስ አገራት ውሃውን በፍትሃዊነትና በተገቢ ሁኔታ እንዲጠቀሙ በማድረግ ረገድ በአገራቱ መካከል ትብብር እንዲጎለብት የተጫወተውን በጎ ሚና ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ የገለፁ ሲሆን ይህ አቋም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የህዳሴ ግድብን በሚመለከት ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያዊያን የልማት አጀንዳ እንጂ የትኛውንም አካል ለመጉዳት ያለመ አለመሆኑን ያስረዱ ሲሆን የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር ጉዳይ ከአፍሪካ ማዕቀፍ ውጪ መፍትሄ ለማምጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።
የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ሲይልቪስተር አንቶኒ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ተቋሙ እንዲጠናከር ጉልህ ሚና እየተወጡ ካሉ አገራት ቀዳሚዋ መሆኗን ያነሱ ሲሆን በቀጣይም ኢኒሼቲቩ የታለመለትን አላማ ለማሳካት በሚያከናውናቸው እንቅስቃሴዎች የኢትዮጵያ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።