ቀጥታ፡

የሸገር ከተማ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና እውቀት መር እንዲሆን የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል - ዶክተር ተሾመ አዱኛ

 

አዲስ አበባ ግንቦት 10 / 2015 (ኢዜአ):- የሸገር ከተማ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና እውቀት መር ከተማ እንዲሆን የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን የከተማው ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ ተናገሩ።

ዶክተር ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችንና የገጠር መንደሮችን በስሩ ይዞ ያሉት የሸገር ከተማ አስተዳደር የተለየ እቅድ ተዘጋጅቶ የተመሰረተ ነው።

ሸገር ከተማ ዓለም አቀፋዊ የከተማ ደረጃን በጠበቀ መልኩ እንዲደራጅ የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል ነው ያሉት።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ሸገር ከተማ የ10 ዓመት እቅድ ያዘጋጀ ሲሆን የመሬት አጠቃቀሙንም በሕግና ስርዓት ለመምራት 'ስፓሻል ፕላን' መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የከተማውን የ10 ዓመት እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የአሰራር መመሪያዎችና ደንቦች ተዘጋጅተው ተጠናቀዋል ብለዋል።

በሌላ መልኩ የሸገር ከተማ አደረጃጀትን የተለየ የሚያደርገው 'ፖሊ ሴንትሪክ' ወይም የከተማዋ ማዕከላት በተለያየ ቦታ የሚገኙበት የከተማ ልማት ስልት መሆኑንም ከንቲባው አብራርተዋል።

በከተማው ስር የሚገኙ እንደ ቡራዩ፣ ሱሉልታና ገላን የመሳሰሉ ከተሞች ቀደም ብሎ የከተማ ማዕከላት የፈጠሩ በመሆናቸው ይህው ይጠናከራል ብለዋል።

ከተማው በርከት ያሉ የከተማ ማዕከላት እንዲኖሩት ከማስቻል ባሻገር እነዚህ የከተማ ማዕከላት፤ ማዕከል ያሰኛቸውን ስራ እንዲያጠናከሩ የሚደረግ መሆኑንም አመላክተዋል።

የሸገር ከተማ መሬት አጠቃቀም ከተለምዷዊ አሰራር በተለየ መልኩ ሰፊው የከተማው መሬት 'ኦፕን ስፔስ' ወይም ከፍት ቦታ ይሆናል ብለዋል።

በዚህም በከተማው 70 በመቶ የሚሆነው ስፍራ ሕዝቦች የሚገናኙበት፣ የሚዝናኑበትና አብሮነትን የሚያጠናክሩበት ስፍራ እንዲሆን መታቀዱን ገልጸዋል።

30 በመቶው የከተማው መሬት ላይ ብቻ የተለያዩ የቤት እና የፋብሪካ ግንባታዎች እንደሚከናወኑበትም አመላክተዋል።

ከተማው ይህን የተለየ እቅድ በአግባቡ ለመተግበር ከ1 ሺህ በላይ አመራርና ከ6 ሺህ በላይ ሰራተኞች በአዲስ መልክ ምደባ መደረጉን አስታውሰዋል።

ከዚህም ባለፈ በከተማ ግንባታ ላይ እውቀት ያላቸው 15 አባላት ያሉት የሸገር ከተማ አማካሪ ቦርድ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም