ቀጥታ፡

የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማሳለጥ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል-ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2015(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ የደረቅ ወደብና ተርሚናል የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማሳለጥ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው ደረቅ ወደብና ተርሚናሉ የሚሰጣቸውን የተለያዩ አገልግሎቶች ተዘዋውሮ ተመልክቷል።


 

የቡድኑ አስተባባሪ እስክንድር አልይ ደረቅ ወደቡ የአገልግሎት ዘርፉን በማዘመንና ደረጃውን የጠበቀ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችሉትን የግንባታ እና የአሰራር ስርዓቶች በመዘርጋት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የደረቅ ወደብና ተርሚናሉ ከድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና በቅርብ ርቀት ላይ እንደመገኘቱ ወደፊት በበርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስተሮች ተቀዳሚ ምርጫ ከመሆን ባለፈ፤ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና ከፍተኛ የስራ ዕድል በመፍጠር በኩል የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በደረቅ ወደብና ተርሚናሉ የሚስተናገዱ አካላትን የስራ እንቅስቃሴ ማሳለጥ የሚያስችሉ የጉምሩክ፣ የባንክ እንዲሁም የጭነት ማስተላለፍ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል እንዲሰጡ መደረጉ የሚበረታታ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል።

በደረቅ ወደቡ የሕፃናት ማቆያ አለመኖር፣ የሰው ኃይል ቁጥር ማነስ፣ የመውጫ በሮች ለጉምሩክ ቁጥጥር በሚሆን የደረጃ ስታንዳርድ ልክ አለመገንባት እና ለአካል ጉዳተኛ የማህበረሰብ ክፍሎች ምቹ የስራ ከባቢን አለማመቻቸት የታዩ ክፍተቶች በመሆናቸው እንዲስተካከሉ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ የደረቅ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ እመቤት ፍሰሃ በበኩላቸው የደረቅ ወደብና ተርሚናሉ በመልቲሞዳል እና በዩኒሞዳል መጓጓዣ የሚመጡ እቃዎችን በወደቡ ተረክቦ ለአስመጪዎች የሚያስረክብ ነው።

ቡናን ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ ባለኃብቶች ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝም ዋና ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በአካባቢው ከሚገኙ ባለኃብቶች ጋር በዘርፉ በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ መነጋገራቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም