በአገር አቀፍ ደረጃ የትራፊክ አደጋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የባለድርሻ ተቋማት ቅንጅት ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል-የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
በአገር አቀፍ ደረጃ የትራፊክ አደጋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የባለድርሻ ተቋማት ቅንጅት ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል-የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2015(ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የባለድርሻ ተቋማት ቅንጅት ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ ።
በመንገድ ደህንነት ዙሪያ የተሻለ ተሞክሮ ባላቸው የኦሮሚያ ክልል ዞኖችና ከተሞች ከሚዲያ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ቡድን የመስክ ምልከታ እያካሄደ ይገኛል።
ቡድኑ በጉብኝቱ በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተከናወኑ ስራዎችን ተመልክቷል።
የአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙንትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ሀምዚያ ጀማል እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ እስካሁን ባለው ሂደት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ23 ሺህ በላይ ከቀላል እስከ ከባድ የትራፊክ አደጋዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ14 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው ያነሱት፡፡
በመሆኑም ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የባለድርሻ አካላት ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የትራፊክ ቁጥጥር እና ግንዛቤ የማስጨበጫ ንቅናቄን ጨምሮ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ጉብኝቱ በዋናነት የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ የተሻለ ስራ ያከናወኑ አካባቢዎችን ልምድ ማስተዋወቅ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
የባሌ ዞን ትራንስፖርት ኤጀንሲ ጽህፈት ቤት ኅላፊ አቶ ተሾመ ለሚ በበኩላቸው የባሌ ዞን ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ከሚያስተናግዱ አካባቢዎች አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል።
ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ህብረተሰቡን ተደራሽ ማድረግ በሚያስችሉ ተቋማትና ቦታዎች በተከናወኑ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ግን አደጋውን መቀነስ እንደተቻለ ገልጸዋል።
ለአብነትም በዞኑ የትራፊክ አደጋ የደረሰ ሞት ከባለፈው ዓመት ሲነጻጸር 60 በመቶው መቀነስ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።
በቀጣይም የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን በማጠናከር በሕይወትና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን አረጋገጠዋል።
የባሌ ሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ እንዳሉት ከተማ አስተዳድሩ መንገዶችን የማስፋት፣ የእግረኛ፣ የተሽከርካሪና የሞተር ሳይክል መንገድ የመለየት ሥራዎችን አከናውኗል።
በተጨማሪም የእግረኛ መቋረጫ የትራፊክ ምልክቶችና የተሽከርካሪ ፍጥነት መገደቢያዎችን መገንባታቸውን ገልጸው፤ ይህም የትራፊክ አደጋ እንዲቀንስ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡