የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በቻይና የናንዣ ግዛት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሀላፊ በሚስተር ሊያንግ ሹን ከተመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በቻይና የናንዣ ግዛት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሀላፊ በሚስተር ሊያንግ ሹን ከተመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2015 (ኢዜአ) ፦ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በቻይና የናንዣ ግዛት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሀላፊ በሚስተር ሊያንግ ሹን የተመራውን የቻይና መንግስት ከፍተኛ የልኡካን ቡድንን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ዘመናትን በተሻገረው የኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች በትብብር መስራታቸውን ያነሱት አቶ አደም ፋራህ ግንኙነቱ ወደተሻለ ደረጃ እንዲያድግ ብልፅግና ፓርቲ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ሁለቱ ሀገራት የፈጠሩት ግንኙነት ከውስጣዊ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የፀዳ ፣በመርህ ላይ የተመሰረተ እንዲሁም እኩልነትን መሰረት ያደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ የቻይና የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየጨመረ መሆኑንና በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉ የቻይና ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ እንደሆነም ተናግረዋል።
በሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ምክንያትም ኢትዮጵያ ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭን በመሰሉ የቻይና መንግስት የልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ መሆን እንደቻለችና ከ90 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ የሚሳለጥበት የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር የዚህ ትሩፋት ተጠቃሽ እንደሆነ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያን በልማታዊ እንቅስቃሴዎች ከመደገፍ በላይ ብድሮችን በማራዘም እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት ቻይና አጋርነቷን እያሳየች እንደሆነ አንስተው ይህንንም ብልፅግና ፓርቲ ልዩ ቦታ እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በቀኝ ግዛት ያልተገዛች እና ለመንግስታቱ ድርጅት ምስረታ ከፍተኛ አስተዋፆ እንደነበራትና ይህንንም በጎ ተፅእኖ በቀጣይ ለቻይና አፍሪካ ግንኙነት መዳበር እንደምትጠቀምበት አንስተዋል።
በቻይና የናንዣ ግዛት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሀላፊ ሚስተር ሊያንግ ሹን በበኩላቸው ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ መልኩ ለመደገፍ የቻይና መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የሲፒሲ እና የብልፅግና ፓርቲ ግንኙነት እንዲጠናከር፣በመንግስታዊ ግንኙነቶችም ኢንቨስትመንቶች ፍሰታቸው እንዲያድግ፣ የንግድ አማራጮች እንዲሰፉ በቀጣይ ሰፊ ስራዎች በቻይና መንግስት በኩል እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።