ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ምቹ መደላድል ተፈጥሯል -ማዕከሉ - ኢዜአ አማርኛ
ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ምቹ መደላድል ተፈጥሯል -ማዕከሉ
ሀዋሳ ግንቦት 09 / 2015 (ኢዜአ) የሀዋሳ የምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማዕከል ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ምቹ መደላድል መፍጠሩን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የሀዋሳ ምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማዕከል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ7ሺ 100 ቶን በላይ ቡና መርምሮ ደረጃ መስጠቱን አስታውቋል።
የማእከሉ አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ሲማ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለስልጣኑ የቡና ጥራትን ለማሻሻል ከሚያከናውናቸው የሪፎርም ሥራዎች መካከል የምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማዕከላትን ማስፋፋት አንዱ ነው።
የሀዋሳ ምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማዕከልም ይህንን ለማሳካት ታስቦ ሚያዝያ 3 ቀን 2015 በይፋ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል።
ይህም ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ምቹ መደላድል በመፍጠር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስተባባሪው አብራርተዋል።
በተለይ የምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማዕከላት መስፋፋትና ለአምራቹ ተደራሽ መሆናቸው ቡና የአካባቢውን ስያሜና ተፈጥሯዊ ይዘት ጠብቆ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል።
ቡናን ገዢ አገሮች የሚፈልጉትን የአካባቢ ዝርያ ቡና በቀላሉ መርጠው ለመግዛትአንደሚያስችላቸው አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።
''በማዕከሉ ከሲዳማ፣ከደቡብና ከኦሮሚያ ክልሎች ተመርቶ ለሚገባው ቡና የጥራት ደረጃ ይሰጣል''ያሉት አስተባባሪው፣ የማዕከሉ መከፈት ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ድረስ የሚደረገውን ጉዞ ከማስቀረት ባለፈ፤ የጊዜና የሀብት ብክነትን ለማዳን አስችሏል ብለዋል።
በማዕከሉ የሚሰጠው የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ የሆነውን ቡና አምራቾቹ ችግሩን በቅርበት በመረዳት ጉድለቱን ለማስተካከል እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለፃ ማዕከሉ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ490 በላይ ቡና የጫኑ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ ከ7 ሺህ ቶን በላይ ቡና መርምሮ የጥራት ደረጃ መስጠቱንና ለውጭ ገበያ ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ መላክ ተችሏል።
በማዕከሉ የጥራት ደረጃ ከወጣለት የተለያዩ አካባቢዎች ቡና ከ70 ከመቶ በላይ የሚሆነው ደረጃ 1 እና 2 መሆኑንም አስታውቀዋል።
በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት መልካም ቢሆንም፤ለሥራ የሚያስፈልጉ ማሽኖች እጥረት፣ የምርት ጥራት ደረጃ ለማግኘት ቡና ጭነው የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ማቆሚያና የቢሮ ጥበት ችግሮች እንዳሉበት አመልክተዋል።
ከተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ጥበት ጋር የተያያዘውን ችግር ለመፍታት ከሲዳማ ክልል ባለድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የማዕከሉ የምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ዴስክ ኃላፊ አቶ የትናየት ሸዋ በበኩላቸው በማዕከሉ የሚሰጠውን የቡና ጥራት ደረጃ ተከትሎ አቅራቢዎችና ላኪዎችን የማገናኘት ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ወቅቱ ቡና ወደ ለውጭ ገበያ ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች የሚገባበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ተገልጋዮች ወደ ማዕከሉ በመምጣት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
በማዕከሉ ህጋዊነቱን የጠበቀ የጥራት ደረጃ የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው "ደረጃቸውን ባልጠበቁት ላይ የጥራት መመሪያ ተከትሎ እርምጃ ይወሰዳል" ብለዋል።
ባለፈው አንድ ወር በተሰራው ሥራ ከደረጃ በታች የሆነ ቡና እንዳልመጣ የተናገሩት ኃላፊው፣ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በማዕከሉ አገልግሎት ለማግኘት ከመጡት መካከል የቡና አቅራቢና ላኪ ወኪል አቶ ታደሰ ደባልቄ በሰጡት አስተያየት ማዕከሉ ተደራሽነትን በማስፋት አቅራቢውንና ላኪውን ተጠቃሚ እንዳደረገ ገልጸዋል።
በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት የቡና ጥራት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸው፣ ጥራቱን ለማረጋገጥ ከማሳ ጀምሮ ተያያዥነት ያለው ሥራ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
"ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ በማዕከሉ ያለውን የቦታ ጥበት ችግር መፍታት ያስፈልጋል "ብለዋል።
''ጥራት ያለውን ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብና የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የማዕከሉ መከፈት ፋይዳው ከፍተኛ ነው'' ያሉት ደግሞ ሌላኛው የላኪና አቅራቢ ተወካይ አቶ ከተማ ካሳ ናቸው።
በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ቀልጣፋ እንደሆነና ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ድረስ የሚደረገውን ጉዞ በማስቀረት ጊዜንና ገንዘብ ለመቆጠብ እንደረዳቸው ገልጸዋል።
በማዕከሉ በተሽከርካሪ ማቆሚያ በኩል የሚስተዋል ክፍተት ሊስተካከል እንደሚገባ አቶ ከተማ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ብቻ ይሰጥ የነበረውን የምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ስራ ለማስፋት ከአንድ ወር በፊት በሀዋሳና ጅማ የምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማዕከላት መክፈቱ ይታወሳል።