ቀጥታ፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን 35 አባላት ያሉት የአማካሪ ኮሚቴ አቋቋመ

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2015 (ኢዜአ):-የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን 35 አባላትን ያቀፈ የአማካሪ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከኮሚቴው አባላት ጋር የትውውቅ መድረክ አካሄዷል።

በኮሚቴው እንዲካተቱ የተጋበዙ ግለሰቦች በተለያየ መልኩ ለኮሚሽኑ ስራዎች ድጋፍ የሚያደርጉ እንዲሁም የተለያየ ልምድና ሙያ ያካበቱ መሆናቸው ተገልጿል።

ኮሚቴው በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እንዲሁም በምክክር ሂደት ላይ ስራዎችን ያከናወኑ ግለሰቦችና የተቋማት ተወካዮችን ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚቴውን ያቋቋመው አዋጅ 1265/2014 ላይ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን መሰረት በማድረግ መሆኑንና ኮሚቴው ስራዎችን የሚያከናውንበት የውስጥ መመሪያ ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ዋና ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በኮሚሽኑ የተከናወኑ ዋና ተግባራትና በቀጣይ ሊሰሩ የታቀዱ ስራዎችን በተመለከተ ለኮሚቴው አባላት ገለጻ ማድረጋቸውን ከኮሚሽኑ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም