ኢትዮጵያ የላፕሴት ፕሮጀክት ራዕይ እውን ለማድረግ ቁርጠኛ ናት -ዶክተር እዮብ ተካልኝ

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2015(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የላፕሴት ፕሮጀክት ራዕይ እውን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ገለጹ።

ሶስተኛው የላፕሴት ኮሪዶር ፕሮግራም የሚኒስትሮች ስብስባ ዛሬ በደቡብ ሱዳን ጁባ ተጀምሯል።

“የላፕሴት ፕሮጀክት ፈጣን ትግበራ ለሰላም፣እድገት፣ዘላቂ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ስብስባ የደቡብ ሱዳን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱ ተገልጿል።

በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ የሚመራው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ልዑክ ኢትዮጵያን ወክሎ በስብስባው ላይ እየተሳተፈ ነው።

ልዑኩ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ፣በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌና በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማሃዲን አካቷል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ኢትዮጵያ፣ኬንያና ደቡብ ሱዳንን በትራንስፖርት የማስተሳሰር አላማ ያለው ላፕሴት ፕሮጀክት ለሶስቱ አገራት የኢኮኖሚና ቀጣናዊ ትስስር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ ራዕይ እውን እንዲሆን ዳግም ቁርጠኝነቷን ታረጋግጣለች ብለዋል።

የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትና የመሰረተ ልማት ክላስተር ሊቀ መንበር ታባን ዴን ጋይ፣የኬንያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ዋና የካቢኔ ፀሐፊ ኪፕቹምባ ሚርኮሜን፣ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተወካዮች የላፕሴት ፕሮጀክት አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል።

በውይይቱ ቀጣናዊ የላፕሴት ኮሪዶር ፕሮጀክት ትግበራን ማፈጠን የሚያስችል ሰነድ እንደሚዘጋጅ ተገልጿል። 

ስብሰባው የመንግስት ልዑካን፣የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣የልማት አጋሮችና የሲቪክ ተቋማትን ያገናኘ መድረክ መሆኑ ተጠቅሷል።

ሶስተኛው የላፕሴት ኮሪዶር ፕሮግራም የሚኒስትሮች ስብስባ እስከ ግንቦት 11 2015 ዓ.ም እንደሚቆይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም