ቀጥታ፡

ኢዜአ በአፍሪካ ቀዳሚ እና አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የጀመረውን ተግባር ማጠናከር አለበት

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2015 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአፍሪካ ቀዳሚ እና አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የጀመረውን ተግባር ማጠናከር እንዳለበት ተገለጸ። 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የሰራተኞች መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ ላይ ይፋዊ የህዝብ ውይይት መድረክ አካሂዷል። 


 

በመድረኩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች እና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ  በዚሁ ወቅት፤ ተቋሙ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መረጃዎችን ለብሮድካስትና ህትመት መገናኛ ብዙሃን ለማድረስ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በአሰራር ራሱን እያደራጀ እንደሚገኝ ጨምረዋል።

የተዘጋጀው ደንብ ኢዜአ ተልዕኮውን ለማሳካት ለጀመረው ለውጥ ከህግ አንጻር ያለውን ክፍተት ለመሙላት፣ ዘርፉን ታሳቢ ያደረገ ስራ ለማከናወንና የሰራተኛና የተቋሙን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚያግዝ ገልጸዋል። 

ተቋሙ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ብቃት ያላቸው ሙያተኞችን ለማግኘት፣ 24 ሰዓት መረጃ ለማድረስ እንዲሁም ግልጸኝትና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ መተዳደሪያ ደንቡ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገሪቱ ባሉት 38 ቅርንጫፎች አማካኝነት ትክክለኛ  እና አስተማማኝ መረጃን ለህትመትና ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን እያደረሰ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የሀገር ውስጥ የመረጃ ምንጭነቱን አጠናክሮ በመቀጠል በጎረቤት ሀገሮች ኬንያና ጅቡቲ ቅርንጫፎችን ለመክፈት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

የተቋሙ አዋጅ ከአስተዳደርና ገቢን ከማመንጨት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ መሻሻሉን ጠቅሰው፤ የሰራተኞች መተዳደሪያ ደንብም ይህንን የሚያግዝ ይሆናል ነው ያሉት።


 

የኢዜአ የስልጠና፣ ምክርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አብዱራህማን ናስር፤ ደንቡ የተቋሙን ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ፣ የሲቪል ሰርቪስ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅና የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎችን አሰራሮችን በማገናዘብ  መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በህዝባዊ ውይይቱ የተገኙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ኢዜአ በምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም በመላው አፍሪካ ቀዳሚ የትክክለኛና አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የጀመረውን ተግባር ማጠናከር እንዳለበት አንስተዋል።

በጎረቤት ሀገሮች ቅርንጫፎችን ለመክፈት እና የመረጃ ተደራሽነቱን ለማጠናከር የጀመረው ተግባር በረቂቅ የሰራተኞች  መተዳደሪያ ደንብ ላይ በአግባቡ መመላከት እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

ከደሞዝ እርከን፣ ልዩ ሙያ ከሚያስፈልጋቸው የስራ መደቦች፣ ከቋሚ ቅጥር የሙከራ ጊዜ፣ ከስራ ሰዓት፣ ከስነምግባር ጉድለትና የተጠያቂነት ሂደትና ሌሎች ድንጋጌዎች ላይም ጥያቄና አስተያየት ተነስቷል።

የተቋሙ ሃላፊዎች በረቂቀ ደንቡ ላይ ከህዝብ መድረኩ ተሳታፊዎች የተነሱ አስተያየቶችን በግብዓትነት በመውሰድ ምላሽ በሚያስፈልጋቸው ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰራተኞች መተዳደሪያ ደንብ በፍጥነት ጸድቆ ስራ ላይ እንዲውል በአስረጅና በህዝብ የውይይት መድረክ የተነሱ ጉዳዮችን አካቶ ለቋሚ ኮሚቴው ማቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ቀደም ሲል በኢዜአ ሰራተኞች መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ ላይ የአስረጂዎች መድረክ ማካሄዱ የሚታወቅ ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ደንቡን በቅርቡ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም