የኮሎምቢያ ምክትል ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሎምቢያ ምክትል ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2015 (ኢዜአ):- የኮሎምቢያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኤሌና ፍራንሲያ ማርኩዌዝ ሚና በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደረሱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፍራንሲያ ማርኩዌዝ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ኮሎምቢያ በሁለትዮሽና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ተገልጿል።
ኢትዮጵያና ኮሎምቢያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር እየሰሩ ይገኛሉ።
ኮሎምቢያ በአዲስ አበባ ኤምባሲ ለመክፈት እንቅስቃሴ መጀመሯም በማሳያነት የሚጠቀስ ነው።
በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት በደቡብ አፍሪካ የጀመሩት ከዛም ወደ ኬንያ ያመሩት ምክትል ፕሬዝዳንት ፍራንሲያ ማርኩዌዝ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት የጉዟቸው የመጨረሻ መዳረሻ ነው።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉት ጉብኝት ኮሎምቢያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለመ መሆኑም ተገልጿል።