በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመታት የሚተገበር ሀገራዊ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ የዕቅድ ማዕቀፍ  ተዘጋጅቷል- የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ

450

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2015(ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ በጦርነት የደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስ ለአምስት ዓመታት የሚተገበር ሀገራዊ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ የዕቅድ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ገለጹ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት ባቀረቡት ሪፖርት፣ የፊስካል ፖሊሲ አስተዳደር ሥርዓትን ማጎልበትና ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም  በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛንን ማስጠበቅ እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትኩረት መደረጉን ጠቅሰዋል።

ለዚህም ለመሰረታዊ ለምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦች፣ ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያ እና  መሰል ምርቶች ከፍተኛ ድጎማ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ለአብነትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ33 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር 15 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከውጭ ሀገር ተገዝቶ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱንም ተናግረዋል።


 

መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ከውጭ ሲገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ ተመርተው ጥቅም ላይ ሲውሉ ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።

የዋጋ ንረቱን በዘላቂነት ለመቀነስ የምርት አቅምን ማሳደግ ተገቢ በመሆኑ መንግስት ከሚያደርገው ድጎማ ባሻገር ሁሉም ለምርትና ምርታማነት ማደግ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም መንግስት በጦርነት የተጎዳውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያገግምና ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት እንዲመለስ የሀገር ውስጥ እና የአጋሮችን አቅም ለመጠቀም ዝግጅት ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር የጦርነትና ግጭት ጉዳት እና የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት አካሂዶ ለመንግስት ማቅረቡንም አንስተዋል።

የደረሰውን ጉዳት በመቀልበስ እና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ እንዲቻል እ.ኤ.አ ከ2023-2028 ድረስ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ አገራዊ የዕቅድ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በማዕቀፉ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ በዕቅዱ መመላከቱንም ነው ያብራሩት ሚኒስትሩ።

ፕሮግራሙን ወደ ስራ ለማስገባት በዓለም ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በተደረገ የርዳታ ስምምነት 300 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ ስራ መጀመሩንም ጠቅሰዋል።

አቶ አህመድ ሺዴ በሌላ በኩል በሪፖርታቸው፤ በመንግስት ስር የሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ይዞታ ለማዛወር፤ የፍላጎት መግለጫ ማስታወቂያ ወጥቶ ከ20 የማያንሱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ኢንቨስተሮች ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል።

ይህን ተከትሎም ድርጅቶቹ እቅዳቸውን እንዲያቀርቡ የሚያስችል ጥሪ ለማድረግ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የስኳር ፋብሪካዎች የዋጋ ትመና ስራው  መጠናቀቁን በማንሳት በቀጣይ ወደግል ይዞታ የማዛወር ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።


 

የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰበሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ  በበኩላቸው  የተጀመሩ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች እና የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት እና የወጭ ፍላጎትን በራስ አቅም የመሸፈን ስራዎችም ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ግጭት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚደረገው ድጋፍ ጉዳቱ ለደረሰባቸው ሰዎች መድረሱን ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም