የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ ያሰለጠናቸውን 119 የኤሌክትሮ ቴክኒካል ኦፊሰሮችን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ ያሰለጠናቸውን 119 የኤሌክትሮ ቴክኒካል ኦፊሰሮችን አስመረቀ
ባህር ዳር ግንቦት 9 / 2015(ኢዜአ)፡- በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ በ21ኛ ዙር ያሰለጠናቸው 119 የኤሌክትሮ ቴክኒካል ኦፊሰሮችን ዛሬ አስመረቀ።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋየ ሽፈራው፤ ዩኒቨርሲቲው ብቃት ያላቸውን የመርከብ ባለሙያዎች በማፍራት ለዓለም ገበያ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአካዳሚው ተመርቀው የመርከብ ባለሙያ በመሆን እያገለገሉ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ምስጉን ሰራተኛ መሆናቸውን ማስመስከር ችለዋል ብለዋል።
ይህም እንደ ሀገር ኢትዮጵያዊያን እድሉን ካገኙ በየትኛውም የሙያ መስክ መስራትና በብቃት መወጣት እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
የተመረቁ የመርከብ ሙያተኞች አሁን ላይ በቬትናም፣ እስራኤል፣ ጀርመን እንዲሁም በኢስያ ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካና የአውሮፓ ኩባኒያዎች እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ተመድበው በሚሰሩባቸው ሃገራትም የሃገራቸውን ገፅታ በመገንባት አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፍራንስ ጆሊበርት በበኩላቸው ፤ ተመራቂዎች በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የመርከብ ባለሙያ ለመሆን የሚያስችል የእውቀትና ክህሎት ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
''ተመራቂዎቹ ከኢትዮጵያ የተገኙ ይሁኑ እንጂ የዓለም ሃብት ናቸው'' ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በቆይታቸው ያገኙትን ሙያ በአግባቡ ተግባር ላይ በማዋል ሀገራቸውንና እራሳቸውን ማስጠራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከተመራቂዎች መካከል ካዴት ይዲዲያ አዲስ በሰጠው አስተያየት፤ ለስድስት ወራት የተሰጣቸው ስልጠና የመርከብ ላይ ኤሌክትሮ ቴክኒካል ኦፊሰርነት ብቁ ባለሙያ እንዲሆኑ ከማስቻል ባለፈ ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ ለመረዳት እድል የፈጠረ ነው ብሏል።
ስልጠናው ማንኛውንም የመርከብ ኤሌክትሪካል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል በተግባርና በንደፈ-ሃሳብ የተደገፈ መሆኑንም አመልክቷል።
በሰለጠነበት ዘርፍም የሃገሩን ስም ከፍ ብሎ እንዲጠራ የሚያደርግ አገልግሎት በመስጠት ሚናውን እንደሚወጣ አስታውቋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡