በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የቴሌፕሪንተር ማሽን ለብሔራዊ ሙዚየም በቅርስነት እንዲቀመጥ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የቴሌፕሪንተር ማሽን ለብሔራዊ ሙዚየም በቅርስነት እንዲቀመጥ ተሰጠ
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2015 (ኢዜአ):-በኢትዮጵያዊው ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ የተሰራው የመጀመሪያው የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ማሽን በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት ለብሔራዊ ሙዚየም በቅርስነት እንዲቀመጥ ተሰጠ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ማሽኑ በብሔራዊ ሙዚየም መቀመጡ ቅርሱ የሕዝብ ሀብት እንዲሆንና ወጣቱ ትውልድ ለፈጠራ ስራ እንዲነሳሳ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ልጅ ኢዛና ተረፈ ቀደም ባለው ጊዜ የቴክኖሎጂ አማራጮች ባልሰፉበት ጊዜ ጥናትና ምርምር በማድረግ የተሰራው ቴሌፕሪንተር አሁን ላይ የተሻለ የቴክኖሎጂ አማራጭ ላላቸው ወጣቶች መነሳሳትን እንደሚፈጥር ተናግሯል።
በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኘውና "የአንኮበሩ ሰው በጄኔቭ" በሚል የኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅን የሕይወት ታሪክ የጻፈው ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ በበኩሉ የፈጠራ ስራው ለወጣቶችና ለታዳጊዎች ማስተማሪያ እንደሚሆን አመልክቷል።
ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ የመጀመሪያውን የአማርኛ ቴሌፕሪንተር በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1950ዎቹ ፈጥረው ከጀርመኑ ሲመንስ የፈጠራ ፓተንት አግኝተዋል።
ኢንጂነር ተረፈ ኢትዮጵያን በቴሌኮም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ልምዳቸውን ከማካፈል ባለፈ በዓለም አቀፉ የቴሌኮሚኒኬሽን ኅብረት የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይነገራል።