ቀጥታ፡

ከአዲስ አበባ አትላንታ የተጀመረው አዲስ የቀጥታ በረራ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን ከጆርጂያና በዙሪያ ካሉት ግዛቶች ጋር ለማስተሳሰር ወሳኝ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2015(ኢዜአ)፦ ከአዲስ አበባ አትላንታ የተጀመረው አዲስ የቀጥታ በረራ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን ከጆርጂያና በዙሪያ ካሉት ጋር ግዛቶች ጋር ለማስተሳሰር ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትላንት ምሽት ከአዲስ አበባ በቀጥታ ወደ አሜሪካዋ ጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ በረራ መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ ወደ አትላንታ የጀመረው የቀጥታ በረራ በሣምንት አራት ቀናት ይደረጋል።

በረራው መጀመሩ አየር መንገዱ በአሜሪካ የሚኖረውን የበረራ መዳረሻ ወደ ስድስት ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።


 

አየር መንገዱ አዲስ አበባን እንደ ዋና ማዕከሉ በመጠቀም አፍሪካዊያን እርስ በእርስ እንዲሁም አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር ለማስተሳሰር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ከአዲስ አበባ አትላንታ የቀጥታ በረራ መጀመሩ ሁለቱ እህትማማች ከተሞች ያላቸውን ሁለንተናዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር አንደሚያስችል ነው የገለጹት።

በተለይም በቱሪዝም፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ያለውን አጋርነት ለማጎልበት ያስችላል ብለዋል።

አትላንታ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ብሎም የአፍሪካ አሜሪካዊያን መቀመጫ መሆኗን አንስተው ይህም ለአየር መንገዱ ሰፊ የገበያ እድልም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

እንዲሁም የበረራው መጀመር አዲስ አበባን ከአትላንታ ብቻ ሳይሆን ከጆርጂያና በዙሪያው ካሉ ግዛቶች ለማገናኘት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።  


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ በቀጥታ አትላንታን ማገናኘት ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።

በሁለቱ ከተሞች መካከል በኢኮኖሚ ትብብር፣ በቱሪዝም መስክ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሰፊ ዕድሎችን ይፈጥራል ነው ያሉት።

የአትላንታ ከንቲባ  አንድሬ ዲከንስ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀመረው በረራ መላው አፍሪካን ከአትላንታ ለማገናኘት ያስችለዋል ብለዋል። 

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን የበረራው መጀመር የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ እንዲሁም በርካታ የአሜሪካን ዜጎች በኢትዮጵያ መኖራቸው የሁለቱ አገራት ጠንካራ ግንኙነት ያሳያል ነው ያሉት።  

የበረራው መጀመር በኢትዮጵያና በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በሰሜን አሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናከር መሆኑን አምባሳደሯ ገልጸዋል።  

በበረራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ግርማ ዋቄና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዛሬው የአትላንታ በረራው 133ኛ የዓለም አቀፍ መዳረሻው ሲሆን በመጪው ሳምንትም ወደ ኮፐንሃገን-ዴንማርክ አዲስ በረራ እንደሚጀምር ገልጿል። 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም