ቀጥታ፡

"ንስሮቹ" ዘጋቢ ፊልም የጸጥታ ተቋማትን አገር የመጠበቅ ጀግንነት እንድንገነዘብ አድርጎናል- ታዳጊዎችና የፊልም ባለሙያዎች

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2015(ኢዜአ)  "ንስሮቹ  ዘጋቢ ፊልም የጸጥታ ተቋማትን አገር የመጠበቅ ጀግንነት እንድንገነዘብ አድርጎናል " ሲሉ በፊልሙ ምረቃ መርሃ ግብር የተገኙ ታዳጊዎች  እና የፊልም ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት አስተባባሪነት የተዘጋጀውና "ንስሮቹ" የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ትናንት ምሽት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣  የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ፣ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የፊልም ባለሙያዎችና ታዳጊዎች በተገኙበት ተመርቆ ለዕይታ በቅቷል፡፡

ፊልሙ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ሲሆን፤  የኢትዮጵያ ጸጥታ ተቋማት የአገርን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የከፈሉትን መስዋዕትነትና ጀብዱ የሚያትት ነው፡፡

በተለይ ታዳጊዎች በምዕራቡ ዓለም በስፋት እንደሚታየው በአገር ፍቅር ስሜት እንዲያድጉና ለአገራቸው ታላቅነት እንዲሰሩ ሞራል የሚፈጥር መሆኑም ነው በፊልም ምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገለጸው፡፡

በመርሃ ግብሩ የተገኙ ታዳጊዎች እንዳሉት፤ ፊልሙ በተለይ እኛ ታዳጊዎች በአገር ፍቅር ስሜት እንድናድግ  የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡


 

ተማሪ ኤደን ዓለማየሁ የብሔራዊ ደህንነት እና የመከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ የጸጥታ ተቋማት አገር ለመጠበቅ በየቀኑ ምን ያህል መስዋትነት እንደሚከፍሉ ተገንዝቢያለሁ ትላለች፡፡

ይህም ታዳጊዎች በቀጣይ በጸጥታ ተቋማት ውስጥ በመቀላቀል አገራቸውን የማገልገል ራዕይ ይዘው እንዲያድጉ የሚያደርግ ነው ብላለች፡፡


 

በተመሳሳይ ተማሪ  ሰሚራ ኡስማን እና ተማሪ ኦላና ዓለማየሁ አገርን ማገልግል ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ስራ ሳይሆን የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ታዳጊዎች አገርን ለማገልግል ከሚመርጧቸው ዘርፎች መካከል የጸጥታ ተቋማት ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ዘጋቢ ፊልሙ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ የኢትዮጵያን የጸጥታ ተቋማትን አቅም እንዲገነዘብና ተቋማቱን የመቀላቀል እቅድ እንዲኖራቸው ያነሳሳል ብለዋል፡፡


 

የሶፍት ዌር ባለሙያ የሆነው ክንፉ አሰፋ በበኩሉ የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ከዚህ ቀደም በነበሩ ስርዓቶች ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘ ጥሩ ስም እንዳልነበረው አስታውሰዋል፡፡


 

አሁን ላይ ግን ተቋሙ ራሱን በማሻሻል የአገርና ህዝብን ደህንነት እና ሰላም ለመጠበቅ ምን ያህል ጀግንነት እየከፈለ መሆኑን በፊልሙ በግልጽ መመላከቱን ገልጿል፡፡

ይህም ለአገር ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ የፊልም ባለሙያ የሆነው ሰለሞን ታፈሰ ዘጋቢ ፊልሙ  በተሻለ የድምጽና ምስል ጥራት የተሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡


 

ከይዘት አንጻርም ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያለውን ተቋማዊ አቅም እንዲሁም አገር በመጠበቅ ረገድ ያከናወናቸውን የጀግንነት ተግባራት በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ነው የተናገረው፡፡

"ንስሮቹ" ዘጋቢ ፊልም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን፤ ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅም ከአንድ ዓመት በላይ እንደወሰደ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም