ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሃዋሳ ከተማ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2015(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ቀን ውሎ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሃዋሳ ከተማ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ51 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ የተቀመጠ ሲሆን ሃዋሳ ከተማ በ32 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል።

ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ ደግሞ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሶስት ጊዜ ተሸንፏል አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን መሪነት ለማጠናከር ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ ወደ ማሸነፍ ለመመለስ የሚያደርጉት መሆኑ ተጠባቂ ያደርገዋል።

ፈረሰኞቹ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፉ ከተከታያቸው ባህር ዳር ከተማ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ከፍ ያደርጋሉ።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ሲዳማ ቡና እና መቻልን ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ያገናኛል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሲዳማ ቡና በ27 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን መቻል በ32 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሲዳማ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በሁለቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት ገጥሞታል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሲዳማ ቡና 2 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም