ቀጥታ፡

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በሕገ መንግሥት መሻሻል ላይ ያደረገውን ጥናት ይፋ አደረገ

 

አዲስ አበባ ግንቦት 08/2015(ኢዜአ)፦የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በሕገ መንግሥቱ ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ያደረገውን ጥናት ይፋ አደረገ።
 
ኢንስቲትዩቱ ˝የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ መሻሻል ይገባዋልን? ከሆነስ ምን ምን ይሻሻል ˝ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት አካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ በሕገ መንግሥቱ ሊሻሻሉ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ የተካሄደ ጥናት ቀርቦ፣ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትና የዘርፉ ምሁራን በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ ለረጅም ዓመታት በስራ ላይ ባለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሻሻል ወይም አለመሻሻል ላይ ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉ ክልሎች ከህብረተሰቡ መረጃ በመሰብሰብ ጥናቱ መካሄዱን ተናግረዋል።

በተለይም ጥናቱ የተካሄደበት ዋና ዓላማ ከሕገ መንግሥት መሻሻል ጋር ተያየዞ በተለያዩ አካላት የሚሰነዘሩ አስተያየቶች የተወሰኑ አካላት ጥያቄ ናቸው ወይስ የህብረተሰቡ የሚለውን መረጃ በማጥናት አስፈላጊውን የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያገኝ ለማስቻል ነው ብለዋል።

በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ የተደረገው ጥናት ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ተያይዞ ለሚኖሩ ውይይቶች እንደግብአት እንደሚረዳም አክለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የሶሻል አንትሮፖሎጂ እና የሕግ ተመራማሪው ዶክተር ደሳለኝ አምሳሉ የጥናቱን ግኝቶች ለውይይቱ ተሳታፊዎች አቅርበዋል።

ጥናቱ ያተኮረው በተወሰኑ የሕገ መንግሥቱ አንቀፆች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥናቱ ስልታዊ የዘፈቀደ ዘዴን በመጠቀም የተካሄደ ሲሆን መረጃውን ለመሰብሰብም 1 ሺህ 687 ሰዎች ተሳታፊ መሆናቸውን አንስተዋል።

አብዛኛዎቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች በሰጡት ምላሽ ሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ያስፈልገዋል ስለማለታቸውም ነው ተመራማሪው የጠቀሱት።

ጥናቱ በሕገ መንግሥቱ የብዝሃነት አያያዝን በተመለከተ የተቀመጡ ድንጋጌዎች መሻሻል እንዳለባቸው ይጠቁማል።

የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ የተወሰኑ ሀሳቦች፣ የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ፣ ብሔራዊ ዓርማ፣ የአስተዳደር ወሰን፣ አንቀፅ 39፣ የፖለቲካ ፓርቲን በብሔር ማደራጀትን በተመለከተ ህገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ የጥናቱ ተሳታፊዎች ፍላጎት እንዳላቸው ጥናቱ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

ጥናቱ ሕገ መንግሥቱን ለመቀየርም ሆነ ለማሻሻል በሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ላይ ተመስርቶ ቢሆን የሚል ምክረ ሀሳብ ማቅረቡን ጠቁመዋል።

ሕገ መንግሥቱ በየትኛውም መንገድ ሲሻሻል አሳታፊ መሆን እንዳለበት ገልጸው፤ ይህም የህዝብ መግባባትን እና አንድነትን ለማምጣት ያስችላል ብለዋል።

ለዚህም በጥንቃቄ የሚከናወኑ እና ጊዜ የሚፈልጉ የውይይት አካሄዶች የተሻለ ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን የተለያዩ ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚያደርጉበት ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልፀዋል።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት 30 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን በመግለጽ ይህም ሕገ መንግሥት በአንቀጽ  104 እና 105 መሰረት የሚቀርቡ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎችን ለማጽደቅ ምን ያህል ድምጽ ያስፈልጋል እና የተደረገው ማሻሻያ በማን ይፀድቃል የሚሉ ድንጋጌዎችን መያዙን ተናግረዋል።

በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ሕገ መንግስትን ከማሻሻል ጋር በተያያዘ ሦስት መሰረታዊ አቋሞች እንደሚንጸባረቁ ገልጸዋል።

እነዚህም "ሕገ መንግሥቱ ምን አይነት ጉድለት የለበትም ምንም ለውጥ አያስፈልገውም፤ ሕገ መንግሥቱ በአጠቃላይ መቀየር አለበት የሚሉ እና ህገ ሕገ መንግሥቱ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ሊደረጉበት ይገባል" የሚሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በረቀቀበት እና ተግባራዊ በተደረገበት ዘመን የነበረውን የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ የወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሕገ መንግሥቱ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ላይ የተለያዩ አካላት ልዩነቶች እንደሚያንጸባርቁ ጠቅሰው፤ ይህንንም ልዩነት በመፍታት የጋራ መግባባት ለመፍጠር በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት አለብን ነው ያሉት።

ለዚህም በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ጥናቶችን መስራት እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ መግባባት የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም