የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ አትላንታ ከተማ የቀጥታ በረራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ አትላንታ ከተማ የቀጥታ በረራ ጀመረ

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ አትላንታ የሚያደርገውን የቀጥታ በረራ ዛሬ በይፋ ጀምሯል።
አትላንታ ከተማም ወደ አሜሪካ በሚደረገው የበረራ መርሃ-ግብር የአየር መንገዱ ስድስተኛ መዳረሻ ሆናለች።
በበረራው ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ የኩባንያው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአትላንታ ከተማ ከንቲባ አንድሬ ዲክንስ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ትሬሲ አን ጃኮብሰንና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብና እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ ወደ አሜሪካ አትላንታ በጀመረው በረራ በሳምንት አራት ቀናት እንደሚያደርግና አትላንታ በአሜሪካ ስድስተኛዋ መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል።
የቀጥታ በረራው መጀመር የሁለቱን እህትማማች ከተሞች ያላቸውን ትስስር የሚያጠናክር እንዲሁም የኢኮኖሚና ማህበራዊ መስተጋብር ለማጎልበት መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን በበኩላቸው የበረራው መጀመር የሁለቱን ከተሞች የኢኮኖሚ ትስስር ከማጠናከር ባሻገር በዲፕሎማሲው መስክም የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የአፍሪካ መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ በቀጥታ አትላንታን ማገናኘት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል።
በሁለቱ ከተሞች መካከል በኢኮኖሚ ትብብር፣ በቱሪዝም፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሰፊ እድሎችን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
የአትላንታ ከተማ ከንቲባ አንድሬ ዲክንስ “በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ በረራ አዲስ አበባን ከአትላንታ ማገናኘት ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካን ከአትላንታ ለማገናኘት ያስችለዋል” ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ ባሉት 144 አውሮፕላኖች ከ140 በላይ የጉዞ መዳረሻዎችን እየሸፈነ እንደሚገኝ አስታውቋል።