በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስተባባሪነት የተሰራው "ንስሮቹ" የተሰኘ ፊልም ለዕይታ በቃ

አዲስ አበባ ግንቦት 08/2015(ኢዜአ)፡- በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስተባባሪነት የተሰራው "ንስሮቹ" የተሰኘ ፊልም ለዕይታ በቃ።

ፊልሙ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተሰመረተ ሲሆን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ጨምሮ የጸጥታ ተቋማት አገርን በመጠበቅ ረገድ ያከናወኑትን ጀብድ የሚተርክ ነው ተብሏል።

በፊልም ምረቃ መርኃ ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በፊልም ምረቃ መርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ የጸጥታ ተቋሞቻችን ኢትዮጵያን በመጠበቅ ረገድ ወዳጅን የሚያኮራ እንዲሁም ጠላትን የሚያሳፍር በርካታ የጀግንነት ታሪክ ሰርተዋል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ፊልሙ አንድ የጀግንነት ታሪክ ላይ ትኩረት አደርጎ መሰራቱን ጠቅሰው ፊልሙ ተሰርቶ ለዕይታ መብቃቱ የጸጥታ ተቋማትን ተቋማዊ ልምድ የቀየረ መሆኑን ገልጸዋል።

ያደጉ አገራት የጸጥታ ተቋማቸውን ገጽታ በፊልም ጭምር እንደሚገነቡ ጠቅሰው ይህ ባህል በኢትዮጵያ ሊጎለብት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በመሆኑም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን የጸጥታ ተቋማት አገር የመጠበቅ የጀግንነት ታሪክ ለህዝብ ለማድረስ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ረገድ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ጥንካሬ በተቋማትና በዜጎች ጥንካሬ ይገለጻል ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ ጠንካራ ተቋማት እንዲፈጠሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።

በተለይም የፊልም ኢንዱስትሪ የኢትዮጵያን የተቋማት ጥንካሬ በዜጎች ልብ ውስጥ የመትከል ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም