በአማራ ክልል ያለውን እምቅ የማዕድን ሀብት ለመለየት በተካሄደ ጥናት አበረታች ውጤት ተገኝቷል- ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ያለውን እምቅ የማዕድን ሀብት ለመለየት በተካሄደ ጥናት አበረታች ውጤት ተገኝቷል- ቢሮው
ባህር ዳር ፤ ግንቦት 8 /2015(ኢዜአ) ፡ - በአማራ ክልል ያለውን እምቅ የማዕድን ሀብት በዓይነት ለይቶ በተገቢው ጥቅም ላይ ለማዋል በተካሄደ ጥናት አበረታች ውጤት መገኘቱን የክልሉ ማዕድን ሃብት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በዚህ ወቅት የቢሮው ሃላፊ አቶ ሃይሌ አበበ ፤ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚው ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ በክልሉ እየተሰራባቸው ካሉ ውስጥ ማዕድን አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ለማዕድን ዘርፉ ልማት እስከ ታች የሚደርስ አደረጃጀት በመፍጠር በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኮንስትራክሽን፣ ብረትና የከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ላይ ከ19 ሺህ 600 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን ጥናት በማካሄድ የማዕድን ክምችት መኖሩን ማረጋገጥ እንደተቻለ አስረድተዋል።
በዚህም ከክልሉ ከሚገኙ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ስምምነት በማድረግ የማዕድን ዓይነት፣ ክምችትና ጥራት ለመለየት በተካሄደ ጥናትም አበረታች ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል።
ከተገኙት ማዕድናትም ወርቅ፣ "ኦፓል" ፣ "አምበር"፣ "ሲልካ ሳንድ"፣ ብረት፣ እብነ በረድና የድንጋይ ከሰል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ከዚህም ሌላ በበጀት ዓመቱ 33 ሺህ ኪሎ ግራም ያልተዋበና የተዋበ የኦፓል ማዕድን ለማዕከላዊ ገበያና ከ84 ነጥብ ዘጠኝ ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ መቅረቡንም አመልክተዋል።
በማዕድን ዘርፉም ከ32 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ሃላፊው አብራርተዋል።
በውይይት መድረኩ ከተሳተፉት መካከል የምዕራብ ጎጃም ዞን ማዕድን ሃብት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጌትነት የኔአባት በበኩላቸው፤ በዞኑ የወርቅ፣ "ግራናይት ሲልካስ"፣" ኳርቲዝ" እና እብነ በረድን ጨምሮ ከ22 በላይ ማዕድናት ዓይነት እንዳሉ በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል።
በዚህም 60 የሚሆኑ ባለሃብቶች በማዕድን ልማት ዘርፍ በመሰማራት ለዞኑ ብሎም ለክልሉና ለሀገሪቱ የኮንስትራክሽን እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሶስት ሺህ 30 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመው ከዘርፉ 8ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡንም አመልክተዋል።
በዞኑ 26 ዓይነት ማዕድናት እንደሚገኙ ዘንድሮ በተደረገ ጥናት መታወቁን የገለጹት የደቡብ ወሎ ዞን የማዕድን ሃብት መምሪያ ሃላፊ አቶ አህመድ አበባው ናቸው።
የኦፓል ማዕድን በወረኢሉ፣ አርጎባ፣ ኩታበር፣ መቅደላ፣ ተንታ፣ አምባሳልና ሌሎች ወረዳዎች ጭምር የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ በወረኢሉ ወረዳ የሚገኘውን ኦፓል የማልማት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በባህር ዳር ከተማ ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይት ላይ ከክልል፣ ዞንና ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።