ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን የግብርናውን ዘርፍ ዕድገት የሚያፋጥኑ ሥራዎችን በትኩረት ሊሰሩ ይገባል - ዶክተር ለገሰ ቱሉ

አዲስ አበባ ግንቦት 08/2015 (ኢዜአ)፡- መገናኛ ብዙኃን  የግብርናውን ዘርፍ ዕድገት የሚያፋጥኑ ሥራዎችን በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ። 

የኮሙኒኬሽን፣ መገናኛ ብዙኃን አመራሮችና ባለሙያዎች በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ያለውን የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይን ጎብኝተዋል።

በአውደ-ርዕዩ በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጅምሮችና ውጤቶች ለዕይታ ቀርበዋል።   

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ በግብርናው መስክ በተለያዩ ዘርፎች የተገኙ ስኬቶች እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴና መሰል ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

በግብርናው ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችና በመስኩ መዋቅራዊ ሽግግር ላይ የተያዙ ውጥኖችንም ለኮሙኒኬሽንና መገናኛ ብዙኃን አመራሮችና ባለሙያዎች ገልጸዋል። 


 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በግብርናው መስክ ተጨባጭ ለውጦች እያስመዘገበች ነው።     

በተለይም ግብርናን የማሳደግ ጥረቱ ፍሬ እያፈራ መሆኑን አመላካች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ገበያ-መር አመራረት ዘዴን መጀመሩ፣ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ መተካት መቻሉ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ የውጭ ምንዛሬ እየተገኘ መሆኑ ለውጤቱ ማሳያዎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።  

ይሁን እንጂ አገሪቷ ካላት ሰፊ የመሬት ኃብት፣ "ተስማሚ አየር ጸባይና ምቹ ሁኔታ አኳያ ገና ብዙ ይቀረናል፤ ይህንን ክፍተት ለመሙላት መገናኛ ብዙኃኑ የበኩሉን ድርሻ መወጣት" አለበት ሲሉ ተናግረዋል።     

በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ሊያዘምኑ የሚችሉ የፈጠራ ውጤቶችን ማስተዋወቅ፣ ተደራሽ እንዲሆኑ መሥራት ላይ መገናኛ ብዙኃን ዘርፉ ሊረባረብ እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ግብርናው ዘርፍ  ምን እየተሰራ ነው? ምን ለውጦች አሉ? የሚለውን ሕዝቡ በሚገባ መረጃ እንዲኖረው መገናኛ ብዙኃን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል። 

የጥናትና ምርምር ሥራዎች መሬት ወርደው ግብርናው ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ እንዲሆኑ መገናኛ ብዙኃን መሥራት እንደሚኖርባቸውም አመልክተዋል።    

ከዚህም አንጻር የሚመሩት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ሕዝቡን በማስገንዘብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ነው የገለጹት። 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን /ኢቢሲ/ ምክትል ሥራ አስፈጻሚና የሬዲዮ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ያኒያ ሰዒድ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙኃን ግብርናን በተመለከተ ሁነቶችን ጠብቆ ከመዘገብ በዘለለ ቀጣይነት ያለው ሥራ በማከናወን የዘርፉ ማነቆዎች እንዲፈቱ የድርሻቸውን ማበርከት አለባቸው ብለዋል። 

ተቋማቸው ከዚህ ቀደም በዘርፉ ሲያከናውን የቆየውን ሥራዎች በቀጣይም አጠናክሮ በመቀጠል የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ይወጣል ነው ያሉት።   

 የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን /አሚኮ/ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰጠኝ አቦሃይ በበኩላቸው፤ ከለውጡ ወዲህ ውጤታማ እየሆነው የመጣው የሌማት ትሩፋት ዙሪያ መገናኛ ብዙኃን በቂ ሥራ ሰርተዋል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።  

የሌማት ትሩፋት ሕብረተሰቡ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ማሳየት በስፋት መሥራት አለብን ሲሉም አክለዋል።           

በተለይም በዓሳ ሀብት ልማት ላይ ኃይቆችና ወንዞች በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግሮች ሳቢያ ዓሳ ልማቱ ፈተና እንደገጠመው አስታውሰው፤ መሰል ፈተናዎች እንዲታለፉ መገናኛ ብዙኃን ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።   

  

 

    

 

 

 

 

 

 

 

 

 

   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም