ቀጥታ፡

የደም ባንኮች ደም ከመሰብሰብ ባለፈ የደም ተዋጽኦ ውጤቶች ጥራትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል--የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት


አዲስ አበባ ግንቦት 8/2015(ኢዜአ):- የደም ባንኮች ደም ከመሰብሰብ ባለፈ የደም ተዋጽኦ ውጤቶች ጥራትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚኖርባቸው ተጠቆመ።


የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ከክልል የጤና ቢሮ ተጠሪዎች፣ ከቅርንጫፍ የደም ባንክ ኃላፊዎችና ዳታ ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል።


 


የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ከመንግስትና ከግል ጤና ተቋማት መስፋፋትና ከአዳዲስ የሕክምና አገልግሎቶች መጀመር ጋር ተያይዞ የደምና የደም ተዋጽኦ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።


እንዲሁም የኮርኒያ ንቅለ ተከላ ፈላጊዎች መበራከትና የዓይን ባንክ አገልግሎት መጠናከር በማስፈለጉ ምክንያት በአዋጅ 528/2015 የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ተብሎ በአዲስ መልክ መደራጀቱን ገልጸዋል። 


አገልግሎቱ እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሰራሮችን ታግዞ እየሰራ ነው ብለዋል።


የደም ለጋሾች፣ የሜዲካል፣ የላብራቶሪና ሌሎች አገልግሎቶችን ማሻሻል የተቋሙ ዋነኛ ትኩረቶች መሆናቸውን ነው አቶ ሀብታሙ ያስረዱት።


በክልል የሚሰሩ የደም ባንኮችና የሚመለከታቸው አካላት ከኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጋር በትብብር እንዲሰሩ አሳስበዋል።


የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት የጥራት እና ሜዲካል ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጤናዬ ደምሴ በበኩላቸው የደምና የደም ተዋጽኦ ውጤቶችን ደህንነትና ጥራት ለማስጠበቅ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ጥያቄዎች መኖራቸውንና ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት በቴክኖሎጂ የማደራጀቱ ጉዳይ እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።


ሁሉም የደም ባንኮች ደም ከመሰብሰብ ባለፈ የደም ተዋጽኦ ውጤቶች ጥራትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ባንኮቹ ለብቃት ማረጋገጫ (አክሪዲቴሽን) ትግበራ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው አመልክተዋል። 


የጤና ሚኒስቴር በጀትን ጨምሮ ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ችግሮች እየተፈቱ መሆናቸውንና በመጪው ጊዜ የተሻለ ስራ ለመስራት መንቀሳቀስ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።


በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም የቀረበ ሲሆን 250 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰቡ በሪፖርቱ ላይ መገለጹን የጤና ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጽ ባወጣው መረጃ አመልክቷል።


በተያያዘም የዓይን ባንክ አገልግሎትን አስመልክቶ የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ የቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ፣ የክልል የደም ባንኮች የድጋፍና ክትትል ሪፖርቶችም ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም