ቀጥታ፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በየዓመቱ የሚያዘጋጀው 10ኛው የመስተንግዶና የክህሎት ሳምንት ተከፈተ

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2015(ኢዜአ):- የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በየዓመቱ የሚያካሄደው 10ኛው የመስተንግዶና የክህሎት ሳምንት በአዲስ አበባ ተከፍቷል፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በየዓመቱ የሚያካሄደውን መርሐ-ግብር የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በይፋ አስጀምረውታል፡፡

የቱሪዝም ዘርፍ በመንግስት ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።

በዘርፉ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ብቃት ያለው የሰው ኃይል መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ኢንስቲትዩት ባለፉት 54 ዓመታት በዘርፉ በርካታ ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ ማስቻሉን አመልክተዋል።


 

የቱሪዝሙን ገበያ በማወቅና አገር በቀል ሀብቶችን በመጠቀም ቱሪዝሙን ተወዳዳሪ ለማድረግ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው በ10ኛው የመስተንግዶ እና የክህሎት ሳምንት ውድድሮች፣ አውደ ርዕዮችና ኮንፈረንሶች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።

ሆቴሎች ባለሙያዎችን የሚመለምሉበት እድል መመቻቸቱን ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

"ክህሎት ለተወዳዳሪነት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የመስተንግዶ እና የክህሎት ሳምንት እስከ ነገ እንደሚቆይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም