ቀጥታ፡

የጤና ሚኒስቴርና የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ የሕክምና ስፔሻላይዜሽንን ማጠናከር የሚያስችል የ5 ሚሊየን ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ   

አዲስ አበባ ግንቦት 08/2015 (ኢዜአ)፡-የጤና ሚኒስቴርና የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ የሕክምና ስፔሻላይዜሽንን ማጠናከር የሚያስችል የ5 ሚሊየን ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ፡፡   

የፕሮጀክቱን ስምምነት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ተፈራርመዋል፡፡ 

በስምምነቱ መሰረትም የአውሮፓ ሕብረት "ከስፓኒሽ እና ጣሊያን  ኮኦፐሬሽን" ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ዘጠኝ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የስፔሻላይዜሽን ተማሪዎችን እና አስተማሪዎችን የሙያ ብቃት ለማሳደግ ይሠራሉ ተብሏል፡፡ 

ፕሮጀክቱን ይፋ የማድረግ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት፤  የጤናውን ዘርፍ የበለጠ ለማጠናከር ለሰው ኃይል ግንባታው ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

በዚህም ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጀምሮ በየደረጃው ያለውን የሰው ኃይል ለማብቃት ከሥልጠና ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ  ድጋፎች በመደረግ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

የስፔሻላይዜሽን ሕክምና ሥልጠናን ማስፋት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሊያ፤ በአሁኑ ግዜም በ22 የትምህርት ተቋማት የስፔሻላይዜሽን ፕሮግራሞች በመሰጠት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።


 

በዛሬው ዕለት የአውሮፓ ሕብረት ይፋ ያደረገው ፕሮጀክትም በዘጠኝ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙ ስፔሻሊስት ሃኪሞችን አቅም ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ስምምነት መሰረትም የአውሮፓ ሕብረት "ከስፓኒሽና ጣሊያን ኮኦፐሬሽን" ጋር በመተባበር በ5 ሚሊየን ዩሮ በጀት ሥልጠናዎችን የማስፋት፣ ቁልፍ የሆኑ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችን ጥራት ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል፡፡ 

በሌላ መልኩም ከእነዚህ አገራት ባለሙያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በማስመጣት የልምድ ልውውጥ ተግባራት እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ለሕክምና ዶክተሮች ሥልጠናን ጨምሮ የአቅም ግንባታ ሥራዎች የሚተገበሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡    

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም