አራተኛውን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው -ፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 08/2015 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ አራተኛውን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባው የፕላንና ልማት ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ  ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

አገራዊ የልማት ዕቅድ ዝግጅትና አፈጻጸም፣ ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም የሚተገበር የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ዝግጅት፣ የልማት ተጠቃሚነትና የመሰረተ-ልማት ሥርጭት ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን አቅርበዋል።

የስነ-ሕዝብ ጉዳዮች ከአገራዊ የልማት ፖሊሲ ዕቅድ ጋር ከማጣጣም፣ ከአሥር ዓመት የልማት ግቦችና ሌሎች ዋና ዋና  ተግባራት ላይ የተከናወኑ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አቅርበዋል።

የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ከምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያየቶች ተነሰተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት አራተኛውን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መቼ ለማድረግ እንደታሰበ ጥያቄ አንስተዋል።

በተጨማሪም የፕሮጀክቶች አፈጻጸምና ክትትል፣ ፍትሃዊነትን ከማረጋገጥ፣ ከልማት ፕሮጀክቶች ልየታ፣ ከአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አንስተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ለጥያቄዎቹ በሰጡት ምላሽ፤ ቀደም ሲል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በአንድ ጊዜ በሁሉም ቦታ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ በተፈጠሩ ችግሮች ሳይካሄድ መቆየቱን አውስተዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ አራተኛውን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም.ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት  የሚተገበር የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ዝግጅት ውስጥ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ትኩረት ከተሰጣቸው ውስጥ እንደሆነ ጨምረዋል።

ከልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አንጻርም እንደየ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ በዘላቂነት ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፎችን በጥናት በመለየት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በተመለከተ ቀደም ባሉት ዓመታት ፕሮጀክቶች ሲቀረጹ ተፈጻሚነታቸውና አዋጭነታቸውን ያላገናዘበ በመሆኑ ለዘመናት ሲጓተቱ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

በመሆኑም የተጀመሩትን በማጠናቀቅ አዲስ የሚጀመሩት አዋጭነታቸውና አስፈላጊነታቸውን በጥናት በመለየት እየተሰራ እንደሆነ ጨምረዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መንግሥት የግብርና የማምረቻው ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ከውጭ በማስገባት አቅርቦትን ለማሳደግ ያከናወነውን ተግባራት ዘርዝረዋል።

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ፤ ሚኒስቴሩ እንደ ሀገር የተናበበ የልማት ፖሊሲ ለመቅረጽ ያከናወነው ተግባር በጥንካሬ ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በቀጣይ የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ ትግበራን ትኩረት ሰጥቶ መከታተል እንዳለበት አሳስበዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም