ቀጥታ፡

ኩታ ገጠም እርሻ ጊዜን በመቆጠብና ብክነትን በመከላከል ተጠቃሚ እያደረገን ነው- የሲዳማ ክልል አርሶ አደሮች

ሐዋሳ  ግንቦት 8/2015(ኢዜአ) የኩታ ገጠም እርሻ ከግብዓት አጠቃቀም እስከ ምርት አሰባሰብ ብክነት እንዳይኖር በማድረግ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን የሲዳማ ክልል አርሶ አደሮች ገለጹ። 

በቆሎ አምራች በሆነው ሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ 17 ሺህ 241 አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም በቆሎ እያመረቱ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል። 

በሲዳማ ክልል በበልግ ከሚለማው የእርሻ መሬት ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በበቆሎ የተሸፈነ ሲሆን፣ ሃዋሳ ዙሪያና ብላቴ ደግሞ ከክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ በበቆሎ አምራችነታቸው የታወቁ ወረዳዎች ናቸው። 

በወረዳዎቹ በሚገኙ ውስን ቀበሌዎች በቆሎ እስከ ግንቦት ወር አጋማሽ መዘራቱን ተከትሎ በሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ የሳማ ኤጅርሳ ቀበሌ አርሶ አደሮችን ኢዜአ አነጋግሯቸዋል። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል አርሶ አደር ሄኖክ ቦኬ እርሳቸውን ጨምሮ 118 አርሶ አደሮች በማቲቾ ክላስተር 56 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ በኩታ ገጠም እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል። 

ላለፉት ሦስት ዓመታት የተለያዩ ሰብሎችን በኩታ ገጠም የማልማት ልምድ እንዳላቸው የገለጹት አርሶ አደሩ፣ "በኩታ ገጠም ማልማት ከግብዓት አጠቃቀም እስከ ምርት አሰባሰብ ብክነት ሳያጋጥም ተገቢውን ጥቅም ያስገኝልኛል" ብለዋል። 

በዘንድሮው የበልግ እርሻ ከወረዳው ያገኙትን ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በአግባቡ ተጠቅመው ወደ ዘር ሥራ መግባታቸውንና መሬቱም በቆሎ ለማልማት ምቹ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል። 

የእርሻ መሬታቸው ኩታ ገጠም በመሆኑ መሬቱን በትራክተር ማረሳቸውን የገለጹት አርሶ አደር ሄኖክ፣ በኩታ ገጠም በጋራ መስራት ጉልበትን ከመቆጠብ ባለፈ የተለያዩ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልጸዋል። 

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታ ገጠም ማልማት መጀመራቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አርሶ አደር ዘገዬ ላንቃሞ ናቸው። 


 

ከዚህ ቀደም በተናጠል አምርተው በሄክታር እስከ 56 ኩንታል በቆሎ ያገኙ እንደነበር ጠቅሰው፣ "በኩታ ገጠም ማልማት ከዚህ በላይ ምርት እያስገኘልን ነው" ብለዋል። 

አርሶ አደሩ እንዳሉት በወረዳው ግብርና በኩል የቀረበላቸውን ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመው በበልግ እያለሙት ካለው በቆሎ በሄክታር ከ70 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሰሩ ነው። 

የሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መረቀ ቶንሲሳ ወረዳው በቆሎ አምራች በመሆኑ በተለይ አርሶ አደሮች የበልግ ወቅትን በጉጉት እንደሚጠብቁት አመልክተዋል። 


 

በወረዳው በበቆሎ ከተሸፈነው 10ሺህ 276 ሄክታር መሬት ውስጥ 7ሺህ 602 ሄክታር በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን ነው የተናገሩት። 

የወረዳው 17ሺህ 241 አርሶ አደሮች በ157 ክላስተሮች ተከፋፍለው በኩታ ገጠም በማልማት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊው፣ "በበልግ ወቅት በበቆሎ ከለማው እርሻ እስከ 500 ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል" ብለዋል። 

በወረዳው ለልማቱ የተለዩ ስምንት ቀበሌዎች አስቀድመው በቆሎ የዘሩ ሲሆን፣ ዘግይተው መዝራት በሚጀምሩ ቀሪ ቀበሌዎችም ሰሞኑን ወደ ዘር ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል። 

ላለፉት ሶስት ዓመታት እየተከናወነ ያለው የኩታ ገጠም እርሻ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ፣ ወረዳው በቆሎ ለማምረት ያለውን ተስማሚነትና ምርታማነት ለማስተዋወቅ ዕድል መፍጠሩን ኃላፊው አስረድተዋል። 

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በክልሉ በበልግ በዋናነት የሚለማውን በቆሎ በኩታ ገጠም በማልማት ግብርናን የማዘመን ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

በክልሉ ሃዋሳ ዙሪያ ወረዳን ጨምሮ በከፍተኛ ደረጃ በቆሎ በሚያለሙ ሌሎች ወረዳዎች አርሶ አደሩን በክላስተር በማደራጀት በትራክተር ጭምር እንዲያመርቱ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። 

በኩታ ገጠም በማረስ እንዲሁም የእርሻ ሥራውን ሜካናይዝድ በሆነ መልኩ በማከናወን ውጤታማ ለመሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው ያብራሩት። 

በክልሉ በበልግ ወቅት እየለማ ካለው ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ የበቆሎ ማሳ 40 ከመቶው በኩታ ገጠም መልማቱንም ኃላፊው አክለው ገልጸዋል። 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም