ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም የብዝሃ ማንነቶችና ባህሎችን ለማጽናት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ሊንከባከበው እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም የብዝሃ ማንነቶችና ባህሎችን ለማጽናት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ሊንከባከበው እንደሚገባ ተመለከተ
ሶዶ፤ ግንቦት 8 /2015 (ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያ የምትከተለው የህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት የብዝሃ ማንነቶችና ባህሎችን በማጽናት ለዘላቂ ሰላምና አንድነት ምሰሶ በመሆኑ ሁሉም ሊንከባከበው እንደሚገባ ተመለከተ።
የሕገ-መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ከደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ጋር በመተባበር ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝምና የመንግስታት ግንኙነት ላይ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄዷል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ባደረጉት ንግግር ፤የህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ህዝቦች ተዋደውና ተከባብረው እንዲኖሩ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የብዝሃ ማንነቶችና ባህሎችን በእኩልነት በማጽናትና በማበልጸግ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት መሠረት መሆኑን አስረድተዋል።
የሚያጋጥሙ ችግሮችንም ተማምኖና ተቀራርቦ በመወያየት ለመፍታት እንደሚያስችልም አውስተዋል።
በተለይ በሀገሪቱ የሚገኙ ቋንቋዎች፣ ፖለቲካዊ አመለካከቶች፣ ብዝሃ ባህልና ኃይማኖቶችን አፅንቶ ለማስቀጠል ወሳኝ በመሆኑ ለህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ማደግና ማበብ ሁሉም ሊተጋ እንደሚገባ አመልክተዋል።
አሁን ላይ የብሔር ማንነትና ሀገራዊ አንድነትን ሊጎዱ የሚችሉ አስተሳሰቦችና እንቅስቃሴዎችን ፈጥኖ በማረም ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የግንዛቤ መድረኩም ይህንን ስራ ይበልጥ አጎልብቶ ለማስቀጠል እንዲያግዝ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው፤ የህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ህዝቦች ፍላጎቶቻቸውን ታሳቢ ያደረገ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው አስችሏል ብለዋል።
ይህን እድል በመጠቀም ዘረኝነትንና ጎሰኝነትን መሰረት ያደረጉ ጥላቻና ግጭቶች ለማምከን ሥርዓቱን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የፌዴራል ስርዓትን ማጎልበት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ዕውን ለማድረግ ይረዳል ያሉት ደግሞ ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የደቡብ ክልል የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጎበዜ ጎኣ ናቸው።
የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ከአስተዳደርና አፈጻጸም ጋር የሚገጥሙ የአተገባበር ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜን ጨምሮ ከክልልና ከዞን የተውጣጡ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና አመራሮች እንዲሁም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ተሳትፈዋል።