የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ለመስራች የግልና የመንግስት ባለአክሲዮኖች ኢንቨስትመንት በይፋ ተከፈተ


አዲስ አበባ ግንቦት 8/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ለመስራች የግልና የመንግስት ባለአክሲዮኖች ኢንቨስትመንት በይፋ ተከፍቷል።

ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የባንኮች እና ኢንሹራንስ ተቋማት ሃላፊዎች እና የቦርድ አባላት የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ ያተኮረ መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። 


የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱራህማን ኢድ ታሂርና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። 


 


መንግስት በኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የ25 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ እንደሚኖረው በሚጠበቀው በዚህ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ለሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የባለቤትነት ድርሻ ለመሸጥ ስራ ተጀምሯል።


በመግለጫውም የአክሲዮን እና የብድር (ቦንድ) ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን በሚቀጥለው ዓመት አስተማማኝና ቀልጣፋ በሆነ የዲጂታል የገበያ ስርዓት ለግዥ እና ሽያጭ የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (Ethiopian Securities Exchange-ESX) መንግስትን ጨምሮ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የገበያው የመስራች ባለአክሲዮኖች እንዲሆኑ የሚያስችለውን ስራ አጠናቆ፣ በዛሬው ዕለት በይፋ ወደ ድርሻ ሽያጭ ምዕራፍ መሸጋገሩ ተገልጿል።


የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ባቋቋመው የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አማካኝነት የገበያውን የቢዝነስ ፕላን እና የአዋጭነት ጥናት፣ የገበያ ቅርጽ፣ የአስተዳደር እና የግብይት ህጎች እና መመሪያዎች፣ የማዘጋጀት እና አስፈላጊ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የመለየት ስራዎች ተጠናቀዋል።


የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አካል የሆነውን የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ የማቋቋም ሂደት ወደሚቀጥለው ምዕራፍ የሚያሸጋግር እና ለመስራች ባለአክሲዮኖች ተሳትፎ ክፍት የማድረግ ሂደት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።


ይህም በመጀመሪያ ደረጃ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ላይ ትኩረት ያደረገ ይሆናል ነው የተባለው።


የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት፣ በተለይ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዚህ ታሪካዊ ገበያ የባለቤትነት ድርሻቸውን እንዲያጠናክሩ ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎች መመቻቸታቸው ተገልጿል።


የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ምስረታ ሂደት አስተባባሪ ዶክተር ጥላሁን ካሳሁን "በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፋይናንስ ገበያ ስርዓት ማቋቋም ለዜጎች፣ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች፣ ለተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት የካፒታል ሰነድ ግዥና ሽያጭን የሚያመቻች ሲሆን፤ ለመንግስት፣ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች እንዲሁም ለግል ኩባንያዎች የተጠናከረና የስጋት መሰረቱ የተሰባጠረ የብድር ገበያ መገልገያ አማራጮችን ያቀርባል" ብለዋል።


የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱራህማን ኢድ ታሂር የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያው የመንግስት ትልቅ የሪፎርም አካል ነው ብለዋል። 


 


ገበያው የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ሚና እንደሚያሳድግ ገልጸው፣ ይህም ከ60 ዓመት በኋላ ዳግም የተጀመረ እንደሆነ ጠቅሰዋል።


25 በመቶ የመንግስት ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ቀሪው 75 በመቶ የግል እንዲሆን በተወሰነው በዚህ ዘርፍ፤ ለመንግስትና ለግሉ ዘርፍ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ነው ብለዋል።  

የወቅቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሃራ በታች ሶስተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህ ገበያ ወደስራ ሲገባም የፋይናንስ አማራጮችን በማስፋት ኢኮኖሚያዊ እምርታን ለማምጣት ትልቅ አቅም እንደሚሆን አንስተዋል።


የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ በበኩላቸው የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ማቋቋሚያ አዋጅን መሰረት ያደረገ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ፈቃድ ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል። 


የሰነደ ሙለ ንዋይ ገበያ ለድርሻ ለመስራች ባለአክሲዮኖች ክፍት መደረጉ በ2016 ገበያውን ወደ ሙሉ ስራ ለማስገባት ትልቅ ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸው፣ በዘርፉ ለሚሳተፉ ፈቃድ ለመስጠትም የሕግ ማዕቀፍ እንደተጠናቀቀ ገልፀዋል።


የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አዋጅ 1248/2013 "የሙዓለ ንዋይ ሰነድ ገበያ" ማለት የሰነዶች ሽያጭ፣ ግዥ፣ ልውውጥ፣ የሽያጭ ዋጋ፣ እንዲሁም ክፍያ በቋሚነት የሚፈጸምበት ቦታ መሆኑን ያብራራል።


ኢትዮጵያ የጀመረችው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በሌሎች ሀገራት ካለውና በተለምዶ የስቶክ ወይም የአክሲዮን ገበያ ከሚባለው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም