በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተሰማሩ 132 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች መካከል አንድም ስራውን ያቋረጠ ባለሀብት የለም--ፓርኩ - ኢዜአ አማርኛ
በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተሰማሩ 132 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች መካከል አንድም ስራውን ያቋረጠ ባለሀብት የለም--ፓርኩ
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2015(ኢዜአ) በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተሰማሩ 132 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች መካከል አንድም ስራውን ያቋረጠ ባለሀብት አለመኖሩን የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሉ ኪ ዩዋን ገለጹ።
የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ በዋናነት በማምረቻው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራ እና ለ25 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ነው።
ፓርኩ ስራ ከጀመረ ወዲህ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በተለይም የገቢ አቅምን በማሳደግ እና በኢንዱስትሪ ሽግግር ውስጥ ጉልሀ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሷል።
የፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጅ ሉ ኪ ዩዋን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክን እንቅስቃሴ በመጎብኘት ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በመገምገም ድጋፉን በማሳየቱ እናደንቃለን ብለዋል።
ሆኖም ቋሚ ኮሚቴው በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ ላይ የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክን በተመለከተ የተሳሳቱ መረጃዎች መነሳታቸውን ዋና ስራ አስኪያጁ ለኮሚቴው በጻፉት ደብዳቤ ጠቅሰዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ህጋዊ ውክልና ያልተሰጠው አንድ ሰራተኛ በተሳሳተ መንገድ 51 የውጭ ኢንቨስተሮች የተሻለ ፍለጋ ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን መርጠው ከኢትዮጵያ ወጥተዋል በሚል ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በቋሚ ኮሚቴው ላይ የመረጃ ችግር እንዲፈጠር በማድረጉ አዝነናል ነው ያሉት።
በቋሚ ኮሚቴው ስብሰባ የፓርኩ የአፈጻጸም ሪፖርት የቀረበበት መንገድም ትክክል እንዳልሆነ በማንሳት፤ በፓርኩ ሰራተኛ የተገለጸው መረጃ በሙሉ የፓርኩን አቋም የማያንጸባርቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
በፓርኩ ውስጥ 132 የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሰማርተው እንደሚገኙ እና አንዳቸውም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸውን የማቋረጥ እና ከኢትዮጵያ የመውጣት ፍላጎት እንዳላሳዩ ጠቅሰዋል።
እስካሁን አንድም የኢንቨስትመንት ውልን የማቋረጥ ማመልከቻ እንዳልተቀበለ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ አልሚዎችን እና ኢንቨስተሮችን እየደገፈ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በተለይም የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማትን በማጠናከር፣ በኢንቨስትመንት ማበረታቻ፣ የአዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምዝገባና ፍቃድ በመስጠት፣ በስራ ፈቃድ፣ የመሬት አቅርቦትን ለባለሀብቶች በማመቻቸት በኩል ከሌሎች ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ባለሀብቶችና ስራ ፈጣሪዎች ስለሀገሪቱ የቢዝነስ ሁኔታ የማወቅ እና ባልተነካው የኢትዮጵያ እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጭ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎታቸውን እያሳዩ መሆኑን ገልጸዋል።
"ለተፈጠረው የተሳሳተ መረጃ የመስጠት እና የተግባቦት ጉድለት ይቅርታ እየጠየቅን ኢንዱስትሪ ፓርኩን በሚመለከት በቂ መረጃ ለመስጠት ዝግጁ ነን" ብለዋል።
ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሀገር ልማት እና ኢንቨስተሮችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን በማንሳት፤ በቀጣይም ኢንዱስትሪ ፓርኩን በማስፋፋት ተጨማሪ ባለሀብቶችን ለመሳብ እንደሚሰራ አብራርተዋል።