ቀጥታ፡

በወላይታ ዞን በዘጠኝ ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተሰበሰበ

ሶዶ፣ ግንቦት 08 / 2015 (ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተለያዩ የገቢ አርዕስት 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰቡን የወላይታ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።

 የመምሪያው ኃላፊ አቶ ታምራት በለጠ እንዳሉት በ2015 የበጀት ዓመት እቅድ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት የዘጠኝ ወራት በተደረገው ርብርብ ከተለያዩ የገቢ አርዕስት 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ክንውን ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ20 በመቶ በላይ ብልጫ አሳይቷል ብለዋል።

ለዚህም ደግሞ ያለንን የገቢ አማራጭ በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ የተደረገ ጥረትና ህገወጥ ሥራ ላይ በተሰማሩ የግብር ከፋይ ማህበረሰቦች ላይ የተወሰደው እርምጃ ለተገኘው ውጤት ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም በተደረገው ቁጥጥርና ክትትል ገቢ የማሰባሰብ ስራው ላይ ደረሰኝ ባለመስጠት፣ ገቢያቸውን በአግባቡ ባለማሳወቅና በሌሎች ወንጀሎች ተሰማርተው የተደረሰባቸው 200 የሚጠጉ ነጋዴዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

እነዚህም እያንዳንዳቸው ከ50 ሺህ ብር በላይ እንዲቀጡ የተደረገ ሲሆን የስራ ቦታቸውን የማሸግና ፈቃድ የመሰረዝ እርምጃ የተወሰደባቸው መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም ግብር ሳይከፍሉ የሚሰሩ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር ማስገባቱ ቅድሚያ ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።

አዲስ ግብር ከፋይ ነጋዴዎችን፣ አዲስ ለመኖሪያ የተከራዩ እንዲሁም አዲስ ለንግድ የተከራዩትን የመለየት ስራም በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።

በዚህም በመምሪያው የደረጃ "ሐ" ዕለት ገቢ ግመታ ከቁርጥ ውጪ ነባር የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋይ ብዛት 26 ሺህ በላይ እንዲሁም የቀን ገቢ ግምት የተገመተላቸው ግብር ከፋዮች ብዛት 28 የሚጠጉ መሆኑን አመልክተዋል።

ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ የሚሆነው "መልሶ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ግንባታ የሚካሄድበት በመሆኑ ነው" ያሉት አቶ ታምራት ዜጎች በታማኝነት ወቅቱን ጠብቆ ግብር መክፈልን ባህል ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ይህም በሀገር ልማት ላይ የሚያደርጉት አስተዋጽኦን ከፍ ከማድረጉም በላይ የሚያስመሰግን ተግባር ነው ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በወላይታ ሶዶ ከተማ የመብራት ጌጦች ሽያጭ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ወንድሙ አየለ የደረጃ ''ሀ'' ግብር ከፋይ ሲሆኑ የሚጠበቅባቸውን 80 ሺህ ብር ዓመታዊ ግብር በጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ጊዜውን ጠብቀው መክፈላቸውን ተናግረዋል።

ለምንፈልገው ልማትና መበልፀግ ከግብር የሚሰበሰበው ገቢ ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት አቶ ወንድሙ፤ ዜጎች ወቅቱን ጠብቀው ግብር በመክፈል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሌላኛው በከተማዋ በኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ሽያጭ ስራ የተሰማሩት አስተያየት ሰጪ አቶ መላኩ ሳሙኤል እንዳሉት የሚጠበቅባቸውን 150 ሺህ ብር ዓመታዊ ግብር በወቅቱ መክፈላቸውን ተናግረዋል።

አክለውም በግብይት ወቅት የሰበሰቡትን 400 ሺህ ብር ተጨማሪ እሴት ታክስንም ጭምር በታማኝነት ገቢ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።

"ግብርን መክፈል የዜግነት ግዴታ እንደመወጣት" ስለሚቆጠር ያለማንም ቀስቃሽነት ወቅቱን ጠብቀው በመክፈል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በዚህም "ኩራት ይሰማኛል" ያሉት አስተያየት ሰጪው ልማቱ የራሳችን በመሆኑ ሁሉም ነጋዴ በዚሁ ልክ የሚጠበቅበትን ልወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በዞኑ ባጠቃላይ ከ32 ሺህ በላይ ህጋዊ የግብር ከፋዮች መኖራቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም