ቀጥታ፡

52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ተጀመረ

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2015(ኢዜአ)፦ 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር መጀመሩን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ፡፡

ውድድሩ ዛሬ በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚሲጀመር በሴቶች ርዝመት ዝላይ፣ በወንዶች ከፍታ ዝላይ የፍጻሜ፣ እንዲሁም በ800 ሜትር ወንዶችና ሴቶች ማጣሪያ ውድድሮች ተካሂደዋል።

 ሻምፒዮናው  ከግንቦት 8 እስከ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ታውቋል። 

የውድድሩ ዓላማ በፈረንጆቹ ከታህሳስ 19 እስከ 27 ቀን 2023 ድረስ በሃንጋሪ-ቡዳፔስት ለሚካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶች አቋማቸውን እንዲለኩ እድል ለመፍጠር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮች፣ በክለቦችና በማሠልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠርና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ነውም ተብሏል፡፡
 

ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ በአህጉራዊ፣ በዓለም አቀፍና በኦሊምፒክ የውድድር መድረኮች በመሳተፍ ድል የተቀዳጁ፣ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ ጀግና አትሌቶች ተሳትፈው ያለፉበትና የሚሣተፉበት የውድድር መድረክ መሆኑ የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሻምፒዮናው ሁሉንም የአትሌቲክስ የውድድር ተግባራትን አካቶና ደረጃውን ጠብቆ የሚካሄድ መሆኑም ተገልጿል።

ለአገሪቱ የአትሌቲክስ ስፖርት እድገት የጎላ ሚና የተጫወቱ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳድሮች፣ ክለቦች፣ ተቋማትና ማሰልጠኛ ማዕከላት ምርጥ አትሌቶቻቸውን ይዘው የሚሳተፉበት መድረክ እንደሆነም ቀደም ባሉት ቀናት በፌዴሬሽኑ በተሰጠ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ እየተካሄደ ይግኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም