ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2015(ኢዜአ):-በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

በዚሁ መሰረት ለገጣፎ ለገዳዲ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ለገጣፎ ለገዳዲ በ11 ነጥብ 16ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። በአንጻሩ ፋሲል ከነማ በ34 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ለገጣፎ ለገዳዲ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። በሶስቱ ተሸንፏል በሁለቱ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ ደግሞ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሶስቱ አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ፋሲል ከነማ 3 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ24ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ድሬዳዋ ከተማ በ30 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን በ41 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ ሽንፈት ገጥሞታል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሁለቱ ሲሸነፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 3 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።

በተያያዘም ትናንት በ24ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ አርባ ምንጭ ከተማ ከወላይታ ድቻ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና ከወልቂጤ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በተመሳሳይ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም