ቀጥታ፡

ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ሆኑ

 

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2015(ኢዜአ)፦ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ቡድኑን በጊዜያዊነት የሚመሩ አሰልጣኞችን ዛሬ ማምሻውን ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ቡድኑን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲመሩ ከቆዩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ ቀጣዩን አሰልጣኝ ለመምረጥ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውይይት ማድረጉን ገልጿል።

በዚሁ መሰረት ኮሚቴው በቴክኒክ ዳይሬክተርነት እየሰሩ የሚገኙትን ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ቀጣይ ጨዋታዎችን እንዲመሩ ከውሳኔ ላይ መድረሱን አመልክቷል።

በተጨማሪ ኮሚቴው ኢንስትራክተር ዳንኤልን እንዲያግዙ በፕሪምየር ሊጉ በመስራት ላይ የሚገኙትና በወቅታዊ ውጤታማነት የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል ያላቸውን የባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ምክትል አሰልጣኝ ሆነው እንዲሰሩ መወሰኑን ጠቅሷል።

ፌዴሬሽኑ ለአሰልጣኙ እና ለክለባቸው ባህርዳር ከተማ ጥያቄ አቅርቦ ፈቃደኛ በመሆናቸው ምክትል አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ ገልጿል።

የግብ ጠባቂ አሰልጣኝም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም