ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጂንካ ቅርንጫፍ ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ችግር ፈቺ ተግባራት ማከናወኑን አስታወቀ

ጂንካ፣ ግንቦት 7/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የዞኑን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ።

የጂንካ ቀይ መስቀል ማህበር በአለም አቀፍ ደረጃ ለ76ኛ፣ በአገር አቀፍ ደግሞ ለ65ኛ ጊዜ የሚከበረውን የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ቀንን "ከልብ የመነጨ ሰብአዊነት"  በሚል መሪ ሀሳብ በጂንካ ከተማ አክብሯል።

በዚህ ጊዜ የጂንካ ቀይ መስቀል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ቢሻው ባለፉት ሁለት አመታት ከ54 ሚሊዮን በላይ በሆነ ወጪ ከ450 ሺህ በላይ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ተጎጂ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚደግፍ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።

ለአብነትም የተለያዩ አካላት በማስተባበር ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑት ሐመር፣  በና-ፀማይ እና በባካ ዳውላ አሪ ወረዳዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ በማድረግ 345 አባዎራዎችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል ።

5 ሺህ ሜትር ኪዩብ የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶች፣ በአራት ትምህርት ቤቶች ለእያንዳንዳቸው ባለ 10 ሊትር የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

በድርቁ ምክንያት ከብቶቻቸውን ላጡ 6 ሺህ ያህል እማወራና አባወራዎች 2 ሺህ 100 ፍየሎችን፣ 1 ሺህ 900 ኪሎ ግራም የመኖ ዘር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ለ40 ሺህ እንስሳትም የህክምናና የክትባት አገልግሎት እንዲሰጥ የመድሃኒትና የህክምና መስጪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

በባካ ዳውላ አሪ ወረዳ ከ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ በጀት በመመደብ አራት ማህበራትን በማደራጀት በተራቆቱ አካባቢዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በማከናወን በንብ ማነብ ስራ እንዲሰማሩ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታልና የጎርፍ አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ማህበረሰቡ ለኮሌራ በሽታ እንዳይጋለጥ 28 መፀዳጃ ቤቶች ገንብቶ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃቱን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በዞኑ ባለፉት ሁለት አመታት በጎርፍ፣ በፀጥታ ችግሮች፣ በእሳት አደጋ እና በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በአጠቃላይ በሁለት አመታት ውስጥ ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱ ከ450 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ማድረጉን አመልክተዋል።

የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኛኩማ አስራት፤ ማህበሩ በዞኑ ባለፉት ሁለት አመታት የተከሰቱትን ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በመከላከል እና ቀውሱን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት እንደነበር ገልፀዋል።

ማህበሩ የሰብአዊ ተግባሩን እንዲወጣ በማስቻል ረገድ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ የማህበሩ አባላትን፣ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችንና የረድኤት ድርጅቶችን አመስግነዋል።

ማህበሩ በአሁኑ ሰአት 20 ሺህ የሚጠጋ አባላት ብቻ እንዳሉት ገልፀው፤ የማህበሩን አቅም ይበልጥ ለማጠናከር የአባላቱን ቁጥር ለማሳደግ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም