የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድ ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል - ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድ ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል - ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2015(ኢዜአ)፡- የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድ ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ገለጹ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በ4ኛ እና 8ኛ ክፍል የትምህርት ምዘና እና በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ጥራት ላይ በተካሄዱ ጥናቶች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉትም በሁለቱም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተካሄዱት ጥናቶች በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ መሻሻል ያሉባቸውን ጉዳዮች ያመላከቱ ናቸው፡፡
በጥናቱም ለተማሪዎች ውጤት መዋዠቅ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች መለየታቸውን ጠቁመው፤ በመማር ማስተማር ሂደቱ ጊዜን በአግባቡ አለመጠቀም እና በትምህርት ቤቶች የሚታዩ የመሰረተ ልማቶች አለመሟላትም ከተለዩ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በትምህርት ቤቶች የሚታየው የማማር ማስተማር መሰረተ ልማት ችግር በመንግስት ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ ኀብረተሰቡ በባለቤትነት መንፈስ የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ስለመሆኑም ነው የጠቆሙት፡፡
በኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ49 ሺህ በላይ የመንግስት ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ መንግስት ሁሉንም ትምህርት ቤቶች በመሰረተ ልማት የማሟላት አቅም አንደሌለው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በትምህርት ቤቶች ያለውን የመሰረተ ልማት እጥረት ለመቅረፍ በቅርቡ ህብረተሰቡን ያሳተፈ አገር አቀፍ ንቅናቄ እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይልቃል ወንድሜነህ በበኩላቸው የ4ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲያስመዘግቡ ከተቀመጠው የውጤት ስታንዳርድ ከ50 በመቶ በታች ማስመዝገባቸው በጥናቱ መመላከቱን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ጥናቱ በዘርፉ የሚታየውን ችግር በመፍታት ረገድ በየአከባቢው የሚገኘው የመንግስት አደረጃጀት ህዝብን በማሳተፍ መስራት እንዳለበት ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ ከተሳተፉት ባለድርሻ አካላት መካከል የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱ ሀሰን በትምህርት ቤቶች አስፈለጊ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድ በአገር አቀፍ ደረጃ የአቅም ውስንነት መኖሩን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ህብረተሰቡ ትምህርት ቤቶችን በቀጣይነት መደገፍ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት ያለውን አቅም በማሰባሰብ ትምህርት ቤቶችን ለመለወጥ እየሰራ መሆኑን በመጠቆም፡፡
በተመሳሳይ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅት አስተዳደር ዳይሬክተር ዲናኦል ጫላ፤ ከትምህርት መሰረተ ልማት ማሟላት ባሻገር የመምህራንን አቅም ማጎልበት ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡