ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የምክክር ጊዜያት እንዲኖሩን የሁሉም አጋርነት ያስፈልጋል - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የምክክር ጊዜያት እንዲኖሩን የሁሉም አጋርነት ያስፈልጋል - ኮሚሽኑ
ጅማ ግንቦት 7/2015(ኢዜአ) ፡- ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የምክክር ጊዜያት እንዲኖሩን የሁሉም አጋርነት ያስፈልጋል ሲል የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዛሬ በጅማ ከተማ የምእራብ እና ምስራቅ ወለጋ፣ የቄለም ወለጋና የነቀምቴ ከተማ ተሳታፊዎች በተገኙበት የኮሚሽኑ ውይይት እያካሄደ ነው።
የምክክር ኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት ገብረ ስላሴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት እንደ ሀገር ለመቀጠል የግጭትና የቅሬታ መንስኤ በሆኑ ጉዳዮቻችን ላይ በመምከር መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል።
ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሳተፋበት አካታች የምክክር መርሃ ግብሮች እንዲኖሩን መተባበርና መተጋገዝ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ ይህም በውይይት ችግሮቻችንን ለመፍታት ያግዙናል ብለዋል።
ሴቶች፣ ወጣቶች ፣ሲቪክ ማህበራት፣ ገበሬዎች፣ መምህራን፣ አካል ጉዳተኞች የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎችም የሚሳተፋበት የምክክር ጊዜያት ፍሬያማ እንዲሆኑ የሁላችንም አጋርነት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሀገራችን ከአንዱ ችግር ወደ ሌላው እየተሸጋገረች እንዳትኖር ዘላቂና አስተማማኝ መግባባት ሰፍኖ የሀገር አንድነት እና ሰላምም ተጠብቆ እንዲቀጥል መስራት አለብን ሲሉም አሳስበዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ዘገየ አስፋው በበኩላቸው የኮሚሽኑ ዓላማ አንዱ የሌላውን ጥያቄና ፍላጎት በመነጋገርና ማድመጥ ሀገራዊ መግባባትን ማምጣት ነው ብለዋል።
ያሉብንን ሀገራዊ ችግሮች በመቀራረብ እና በመነጋገር ለመፍታት ያለመ እቅድ ይዞ እየሰራ ያለው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከውይይቱ የሚገኙ ግብአቶች በፖሊሲ ደረጃ ተቀርጸው ለአገራዊ ግንባታ እንደሚውሉ ነው የገለጹት።
በመሆኑም ኮሚሽኑ ለሚያካሂዳቸው ታላቁ ውይይት አሁን እየሰራ ባለው የአጀንዳ ልየታ ውይይት በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 1ሺህ 300 ወረዳዎች ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የተውጣጡ ተሳታፊዎች የሚመረጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች የሚቀርቡ ማናቸውም ቅሬታ፣ ሀሳቦች፣ ጥያቄዎችና ምክሮች ተሰብስበው ለሀገራዊ መግባባቱ የሚያበረክቱት አስተዋጽዎም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በውይይቱ ተሳታፊ ከሆኑት ነዋሪዎች መካከል ከምስራቅ ወለጋ ዞን የመጡት አቶ ተሾመ ቦቦ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ የተኬደበት መንገድም ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣት ወሳኝ በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ፋጡማ ሱሌማን በበኩላቸው በግጭቶች ምክንያት የሚመጡ ስጋቶችን በምክክር መፍታት ብንችል ሰላማችን ይመለሳል ብለዋል።
በጅማ እየተደረገ ያለው የውይይት መድረክ በሚቀርቡ የመነሻ ሐሳቦች መሰረት ተሳታፊዎች በቡድን ተወያይተው ግብዓት ከተሰበሰበ በኋላ ነገ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።